ቀጥታ፡

የህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደቱን ጠብቆ እንዲቀጥል በትኩረት መስራት ይገባል-ጽህፈት ቤቱ

ደብረ ማርቆስ የካቲት 20/2015 (ኢዜአ) የታላቁ ህዳሴ ግድብ በተጀመረበት አግባብ ሂደቱን ጠብቆ እንዲጠናቀቅ ህብረተሰቡን የማነሳሳት ስራዎች ተጠናክሮ መቀጠሉን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ዙር የቅስቀሳ ጉዞ በደብረ ማርቆስ ከተማ ተካሂዷል።

የጽህፈት ቤቱ ተወካይ አቶ ንጉሴ አባተ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት ጽህፈት ቤቱ ከኢትዮጵያ ታሪክ ባህልና ቅርስ አድን በጎ አድራጎት ድርጅት ጋር በመተበባር የህዳሴ ግድብ ጉዞ ተዘጋጅቶ ህዝቡን የማነሳሳት ስራ እየተከናወነ ነው።

የህዳሴ ግድብ ጉዞው ከሳምንት በፊት በአዲስ አበባ የተጀመረ ሲሆን ዛሬ በደብረ ማርቆስ ከተማ ንጉስ ተክለሃይማኖት አደባባይ የንቅናቄና ገንዘብ የማሰባሰብ ተግባር እየተካሄደ ነው።

አሁን ሁለተኛው ዙር ጉዞ እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው፤ በመጀመሪያ የህዳሴ ጉዞ ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን አስታውሰዋል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በተያዘለት የግንባታ ሂደት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በተለያዩ መርሃ ግብሮች ሲካሄድ የቆየው ህብረተሰቡን የማነሳሳትና ሃብት የማሰባሰብ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ታሪክ ባህልና ቅርስ አድን በጎ አድራጎት ድርጅት የህዳሴ ጉዞ ቁጥር ሁለት አስተባባሪ አቶ ነጮ ወርቁ በበኩላቸው የህዳሴ ጉዞ ዓላማ በመላው ኢትዮጵያ በመዘዋወር የህዳሴ ግድቡን እኛው እንደጀመርነው እንድንጨርሰው ህብረተሰቡን በማነቃቃት ገንዘብ ማሰባሰብ ማስቻል ነው ብለዋል።

በዚህ ፕሮግራም የቦንድ ግዥ እና የ8100ኤ መልክት መላክን ጨምሮ የተለያዩ የገንዘብ ማሰባሰቢያ መንገዶች የሚካሄዱ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከዚህ በፊት በተደረገው ጉዞ ከ7 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የሚያካልል 200 ከተሞችን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰው፤ ይህም ህብረተሰቡ ከፍተኛ መነቃቃት ያሳየበት እንደነበረ ገልጸዋል።

አሁን በተጀመረው የህዳሴ ጉዞ ደግሞ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ሃብት ለማሰባሰብ ታቅዶ ከሳምንት በፊት መጀመሩን አስታውቀዋል።

በተደረገው የህዝብ ማነቃቃት ስራም ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ በተለያዩ የገንዘብ ማሰባሰቢያ መንገዶች ገቢ መደረጉን ጠቅሰው፤ ይህ ጉዞ የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚቀጥል መሆኑንም አብራርተዋል።

የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪ አቶ አእምሮ ዘውዴ እንዳሉት ''የህዳሴ ግድብ ለነገ እድገታችን ተስፋ ስለሆነ እገዛ ለማድረግ ወደኋላ አንልም'' ብለዋል።

በእለቱም የ500 ብር ቦንድ እና የህዳሴ ግድቡን አርማ የያዘ ቁልፍ መግዛታቸውን ጠቅሰው፤ ከዚህ በፊትም የአንድ ሺህ ብር ቦንድ የገዙ መሆናቸውን አብራርተዋል።

ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ሀብታሙ አበበ በበኩላቸው ''የአንድነታችን አርማ የሆነው የህዳሴ ግድብ እስኪጠናቀቅ የምችለውን ሁሉ አስተዋጽኦ አደርጋለሁ'' ብለዋል።

ለግድቡ ግንባታ በሚቻለው አቅም ሁሉ መደገፍ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ እርሳቸውም የ300 ብር ቦንድ መግዛታቸውን ገልፀዋል።

ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከህብረተሰቡ ተሳትፎ ከ17 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማሰባሰብ እንደተቻለም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም