ቀጥታ፡

ከአድዋ ጀግኖች የወረስነውን ጀግንነትና ፅናት ሰንቀን የኢትዮጵያን ክብርና አንድነት አናስቀጥላለን-የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ አባላት

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 20/2015 ከአድዋ ጀግኖች የወረስነውን ጀግንነትና ፅናት ሰንቀን የኢትዮጵያን ክብርና አንድነት አስጠብቀን ለቀጣዩ ትውልድ እናስተላልፋለን ሲሉ የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ አባላት አስታወቁ። 

ኢዜአ ያነጋገራቸው የአየር ወለድና ኮማንዶ ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት አባላት "ከአድዋ ድል መተባበርና አንድነትን፣ ጀግንነትን፣ ጽናትንና የአይበገሬነት ወኔን አውርሶናል" ይላሉ። 

ከኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ አባላት መካከል መቶ አለቃ ፋሲል ጌትነት እና መሰረታዊ ወታደር አሸናፊ ሞቱማ፤ ከአድዋ ጀግኖች ዘመንና የጦር መሳሪያ ቢለየንም ዛሬም የሀገር ፍቅር፣ አንድነትና ጀግንነት ወኔ እንደወረሱ ገልጸዋል። 

"በአድዋ ጦርነት የቀደሙት ትውልዶች ለሀገር ክብር ሲሉ በጀግንነት የተዋደቁበትና የኢትዮጵያን ክብርና ሉአላዊነት አስጠብቀው የዘለቁበት ታላቅ የታሪክ አጋጣሚ መሆኑን አስታውሰው፤ እኛም ይህንኑ አስጠብቀን እንቀጥላለን" ሲሉ አረጋግጠዋል።  

በአድዋ ጀግኖች ታላቅ መስዋእትነት ክብሯና ሕልውናዋ ተጠብቆ የዘለቀችውን አገር ለተረካቢ ትውልድ አስጠብቀን እንቀጥላለን ያሉት ደግሞ ወታደር ቢላል ምሳው እና አብዲ ከድር ናቸው። 

የሰራዊቱ አባላት ለኢትዮጵያ ክብርና ሉአላዊነት ዘብ መቆማቸውን በማረጋገጥ በአብሮነት ፅኑ መሰረት ኖሯት ትቀጥላለች ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም