ቀጥታ፡

የአፍሪካ ኤሌክትሮኒክ ትሬድ ግሩፕ በአዲስ አበባ የምስራቅ አፍሪካ ዋና መሥሪያ ቤቱን ሊከፍት ነው

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 20/2015 የአፍሪካ ኤሌክትሮኒክ ትሬድ ግሩፕ በአዲስ አበባ የምስራቅ አፍሪካ ዋና መሥሪያ ቤቱን ለመክፈት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እየተወያየ መሆኑን የግሩፑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙሉዓለም ስዩም ገለጹ።

የአፍሪካ ኤሌክትሮኒክ ትሬድ ግሩፕ በተለያየ ሙያና ስራ ላይ በተሰማሩ አፍሪካውያን ከ14 ዓመት በፊት የተቋቋመ አህጉራዊ የንግድ ተቋም ነው። 

ዋና መቀመጫውን በሩዋንዳ ኪጋሊ ያደረገው ይኸው ተቋም አፍሪካ በዲጂታል የኢኮኖሚ ሥርዓት ውስጥ ያላትን ድርሻ ከፍ ለማድረግ እየሰራ ነው።  

ተቋሙ በተለይም የአፍሪካ የኤሌክትሮኒክስ ንግድ ልውውጥን ለማጠናከር የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች ለመፍጠር ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በትብበር በመስራት ላይ ይገኛል።

የአፍሪካ ኤሌክትሮኒክስ ትሬድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሙሉዓለም ስዩም ለኢዜአ እንደገለጹት ኢትዮጵያ የተቋሙ የምስራቅ አፍሪካ ዋና መስሪያ ቤት እንድትሆን ከሁለት ዓመት በፊት ከ18 አገራት ጋር ተወዳድራ አሸንፋለች።  

ይህንንም ተከትሎ ተቋሙ በአዲስ አበባ የምስራቅ አፍሪካ ዋና መሥሪያ ቤቱን ለመክፈትና ወደ ስራ ለማስገባት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ውይይት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። 

የተቋሙ የምስራቅ አፍሪካ ዋና መቀመጫው አዲስ አበባ መሆኑ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።  

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2030 ከ95 በመቶ በላይ የዓለም ንግድ በሙሉ በዲጂታል ስርዓት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው አፍሪካ ለዚህ መዘጋጀት አለባት ብለዋል።

በመሆኑም በመሰረተ ልማት፣ በሰው ኃይል አቅም ግንባታ፣ በጥናት፣ በዲጂታል ገበያ እና በሌሎች ዘርፎች ተቋሙ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።  

ለአብነትም በአፍሪካ የተሰሩ ምርቶችን ብቻ የሚያበረታታ ‘Sokokuu-Africa’ የተሰኘ አህጉራዊ የኤሌክትሮኒክስ መገበያያ ስርዓት ስራ ላይ ማዋላቸውን ጠቅሰዋል።

ከገንዘብ አቅርቦት ጋር በተያያዘም፤ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ለአነስተኛና መካከለኛ የንግድ ተቋማት የሚያስፈልግ 330 ቢሊዮን ዶላር ክፍተት መኖሩን ጠቁመዋል።

ይህንን ክፍተት ለመሙላት ተቋሙ ከተለያዩ ተቋማት ጋር መስራት የሚያስችል ዓለም አቀፍ የስትራቴጂክ ቢዝነስ ጥምረት ቡድን መመስረቱን አስረድተዋል።

የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከሰኔ 2014 ዓ.ም ጀምሮ የአፍሪካ ኤሌክትሮኒክስ ንግድ ግሩፕን በሊቀ-መንበርነት በመምራት ላይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም