በስራ እና የሰራተኞች ፍልሰት ላይ ያተኮረ የኢጋድ አባል አገራት የሚኒስትሮች ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በስራ እና የሰራተኞች ፍልሰት ላይ ያተኮረ የኢጋድ አባል አገራት የሚኒስትሮች ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 20/2015 በስራ፣ የቅጥር እና የሰራተኞች ፍልሰት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ሁለተኛው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) አባል አገራት የሚኒስትሮች ጉባኤ በአዲስ አበባ ተጀምሯል።
የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አሰግድ ጌታቸው መንግስት የሰራተኞች ፍልሰት እና በስደት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የሚሰሩ ሰራተኞች መብት እንዲጠበቅ ከሚመለከታቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ አጋሮች እና የልማት ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራ ነው ብለዋል።
የሰራተኞች ፍልሰት በአግባቡ ከተያዘ ተቀባዩንና የመጣበትን አገር፣ ፍልሰተኞችንና ቤተሰቦቻቸውን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
ደካማ የፍልሰት አስተዳደር ደግሞ በአገራት እና በፈለሱት ዜጎች ላይ ፈተናዎችን ሊፈጥር እንደሚችል አስገንዝበዋል።
የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን ለመከላከል አገር አቀፍ፣ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ ትብብር እና የተግባር እርምጃ እንደሚያስፈልግ አቶ አሰግድ አስረድተዋል።
ጉባኤው በስራ፣ ቅጥር እና የሰራተኞች ፍልሰት ላይ የኢጋድ አባል አገራት ያላቸውን ትብብር ማጠናከር አላማ እንዳለው ተገልጿል።
እ.አ.አ በ2021 በጅቡቲ በተካሄደው የመጀመሪያ ጉባኤ አገራት የፈረሙትን የስራ፣ የቅጥር እና የሰራተኞች ፍልሰት ድንጋጌ እና የተግባር እቅድ እንደሚገመገም ተነግሯል።
ጉባኤው እስከ የካቲት 23 ቀን 2015 ዓ.ም እንደሚቆይ ተመላክቷል።