ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ድምፅ ሊሆን የሚችል መገናኛ ብዙሃን ሊኖራት ይገባል-ምሁራን

አርባ ምንጭ (ኢዜአ) የካቲት 20/2015 ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ድምፅ ሊሆን የሚችል ጠንካራና ተጽዕኖ መፍጠር የሚችል የመገናኛ ብዙሃን ተቋም ሊኖራት እንደሚገባ ምሁራን ገለጹ።

ተለዋዋጭ የሆነውን የ21ኛውን ክፍለ ዘመን የፖለቲካና ሌሎች ጉዳዮችን በአግባቡ ተገንዝቦ ተጽዕኖ ፈጣሪነትን ለማጠናከር መስራት እንደሚገባም ምሁራኑ ጠቁመዋል።

"በ21ኛው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ሚና በአፍሪካ" በሚል ርዕስ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩም ኢትዮጵያ መከተል ስለሚገባት የውጭ ፖሊሲ ላይ ትኩረት ተደርጎ ውይይት ተደርጓል።

በመድረኩ ላይ የተሳተፉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክልላዊና አካባቢያዊ ልማት ትምህርት ክፍል መምህርና የውይይቱ ተሳታፊ ዶክተር የሺጥላ ወንድሜነህ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫና የፖለቲካ ማዕከል ሆና እያገለገለች ነው።

በመሆኑም ለአፍሪካ ድምጽ ሊሆን የሚችል ጠንካራ የመገናኛ ብዙሃን ተቋም ሊኖራት ይገባል ብለዋል።

ጠንካራ የመገናኛ ብዙሃን ተቋም ያላቸው የዓለም ሀገራት ተቋሙን ተጠቅመው ፍላጎታቸውን በሌላው ላይ በመጫን አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደሩ መሆኑን ገልጸዋል።

በእነዚህ መገናኛ ብዙሃን በተለያዩ ጊዜያት በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ የሚዲያ ዘመቻ ሲደረግ እንደነበር ያስታወሱት ዶክተር የሺጥላ፣ "የእነዚህን ተቋማት የሚዲያ ዘመቻ ሊገዳደርና የአፍሪካን ፍላጎት በማስቀደም ሊመራ የሚችል መገናኛ ብዙሃን ሊኖራት ይገባል" ብለዋል።

እንደ ዶክተር የሺጥላ ገለጻ፣ በአሁኑ ወቅት በፐብሊክ ዲፕሎማሲው ረገድ የእነዚህ ሀገራት ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ትልቅ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ።

ለአብነትም ኳታር፣ ቻይና፣ እንግሊዝ፣ አሜሪካ እና ሩሲያ ለብሔራዊ ጥቅማቸው ጥብቅና የሚቆሙ ጠንካራ ዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋም እንዳላቸው ጠቁመዋል።

This image has an empty alt attribute; its file name is አቶ256-1-1024x577.png

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ደሳለኝ አምባው በበኩላቸው፣ "መገናኛ ብዙሃን ከህግ አውጪ፣ አስፈጻሚና ተርጓሚ ቀጥሎ አራተኛው የመንግስት አካል በመሆኑ ተጽዕኖ ፈጣሪነቱ የጎላ ነው" ብለዋል።

መገናኛ ብዙሃን ለዲፕሎማሲ እንዲሁም ለልማትና ሰላም መረጋገጥ ትልቅ አስተዋጽኦ አንዳለውም ተናግረዋል።

"ኢትዮጵያ የአፍሪካ መዲና ሆና በሚዲያ ብዙ ያልተጠቀመችባቸው ነገሮች አሉ" ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ከዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ጋር ተወዳዳሪ የሆነ የሚዲያ ተቋም በኢትዮጵያ እንዲገነባ ለመንግስት ምክረ-ሃሳብ እንደሚቀርብ ጠቁመዋል።

"ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ እንደመሆኗ መጠን ያላትን ሚና ከፍ አድርገን በማሰማት ዓለም እንዲያውቀው ለማድረግ ተጽዕኖ ፈጣሪ ዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋም ያስፈልጋታል" ያሉት ደግሞ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳምጠው ዳርዛ ናቸው።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ለነፃነትና እኩልነት ብሎም ለልማትና ሰላም የጎላ ሚና እንደነበራት አስታውሰው፣ በቀጣይ ይህንን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ብዙ ሀገራት ከወታደራዊ ሃይል በላይ ለመገናኛ ብዙሃን ልማት ከፍተኛ ትኩረት እየሰጡ መሆኑን ዶክተር ዳምጠው ጠቁመው፣ "ኢትዮጵያም ይህንን በቀላሉ ማሳካት የሚያስችል አቅም አላት" ብለዋል።

በመድረኩ ላይ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩትና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሥራ ሃላፊዎች የተገኙ ሲሆን የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም