ባለፉት ስድስት ወራት ከብልሹ አሰራርና ሌብነት ጋር በተያያዘ ከ200 በላይ አመራርና ሰራተኞች ላይ ክስ ተመስርቷል"-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

1293

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 19/2015 ባለፉት ስድስት ወራት ከብልሹ አሰራርና ሌብነት ጋር በተያያዘ ከ200 በላይ አመራርና ሰራተኞች ላይ ክስ መመስረቱን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም ግምገማ ዛሬ ተጠናቋል።

በማጠቃለያው ወቅት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ብልሹ አሰራርና ሌብነትን የመከላከል ስራ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

አገልግሎት አሰጣጥን ከወቅቱ ጋር እንዲሄድ ለማስቻል በርካታ ዘርፎችን የማዘመን እና የተገልጋዩን እርካታ ለማረጋገጥ የሚያስችል ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ጫናን በመቀነስ የነዋሪውን ችግር እንዲያቀሉ የተጀመሩት የእሁድ ገበያ እና የሌማት ትሩፋት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ጠቁመዋል።

በእሁድ ገበያ ለመሰረታዊ ፍጆታ የሚሆኑ ምርቶች በቀላሉ ህብረተሰቡ ጋር እንዲደርሱ ለማድረግ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አስታውቀዋል።

አስተዳደሩ ከተማዋን ለነዋሪዎች ጽዱ፣ ውብና ምቹ ከማድረግ ባሻገር ዓለም አቀፍ የዲፕሎማቲክ ከተማነቷን የምትመጥን ለማድረግ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ ተግባራዊ እያደረገ ነውም ብለዋል።

ምናልባት የ3 ሰዎች፤ የተቀመጡ ሰዎች፤ የቆሙ ሰዎች እና የቤት ውስጥ ምስል

“ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከር አመራራችን ፅንፈኝነትን፣ ጥላቻን፣ የህብረተሰቡን አንድነት የሚንዱ አስተሳሰቦችን፣ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚደረጉ የሚዲያ ዘመቻዎችንና ሌሎች የፓርቲያችን እሳቤ ያልሆኑ አመለካከቶችን በመዋጋት ረገድ እየተሰራ መሁኑ ተናግረዋል።

“አሁንም ወደ ከተማ የሚደረገው ፍልሰት እና በህቡእ አደረጃጀት የሚደረግ ህገ-ወጥነት ላይ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል” ሲሉ መግለጻቸውን ከንቲባ ጽህፈት ቤት በማህበራዊ ትስስር ገጹ ያሰፈረው መረጃ ያመለክታል።

ምናልባት የ3 ሰዎች እና የተቀመጡ ሰዎች ምስል

በቀሪ የበጀት አመቱ ወራት ያልተከናወኑ ተግባራት ተለይተው በእቅድ ክለሳ እንዲካተቱ በማድረግ የህዝቡን ኑሮ የሚያቀሉ ፕሮጀክቶች ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት እንደሚሰሩም ከንቲባ አዳነች አክለው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም