ስፖርታዊ ውድድሮችን ለቱሪዝም ዕድገት ምንጭ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተጠቆመ

ሀዋሳ (ኢዜአ) የካቲት 19/2015 በኢትዮጵያ ከተሞች ስፖርታዊ ውድድሮችን በማስፋፋት ለቱሪዝም ዕድገት ጉልህ ሚና እንዲጫወት እየተሰራ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።

አትሌቶችን ጨምሮ 3 ሺህ 500 ሰዎች የተሳተፉበት 11ኛው የሶፊ ማልት ግማሽ ማራቶን ውድድር ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ተካሂዷል።

በውድድሩ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሠላማዊት ዳዊት እንዳስታወቁት፤ የተለያዩ ኩነቶችን በማዘጋጀት ቱሪዝምን ለማነቃቃትና ዘርፉ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን ድርሻ ለማሳደግ እየተሰራ ይገኛል።

እስካሁን ከአዲስ አበባ ውጭ በሀዋሳና በቆጂ ስፖርታዊ ውድድር ሲካሄድ መቆየቱን ጠቅሰው፤ በሌሎች የክልል ከተሞች መሰል ውድድሮችን በማስፋፋት የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ ከተማዋ ለስፖርታዊ ውድድሮችና ሌሎች ትላልቅ ኩነቶች ምቹ በመሆኗ ከጊዜ ወደ ጊዜ ለተለያዩ መርሀ ግብሮች እየተስተናገደባትና ቱሪዝሙም እየተነቃቃ እንደሆነ ተናግረዋል።

ስፖርታዊ ውድድሩ ለከተማዋ የቱሪስት ፍሰት ጉልህ አስተዋጽኦ ከማበርከቱም ባሻገር ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት እያገዘ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በየዘርፉ ያሉ ስፖርተኞችን ለሀገር በማበርከት የምትታወቀው ሀዋሳ አገርን የሚወክሉ ስፖርተኞች ለማፍራት የምትሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አዘጋጅ ዳግማዊት አማረ ውድድሩን ስናዘጋጅ በዋናነት የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን የትኩረት ማዕከል በማድረግ ነው ብለዋል።

ከቱሪዝም ኢትዮጵያ ጋር በጋራ እየሰራን ነው ያሉት አዘጋጇ፤ ከተሳታፊዎች መካከል እጣ የደረሳቸው በኢትዮጵያ የተለያዩ የቱሪስት መዳረሻዎችን የሚጎበኙበት ዕድል መመቻቸቱን ገልጸዋል።

በውድድሩ ከግማሽ ማራቶን በተጨማሪ የስምንት ኪሎ ሜትር እንዲሁም የህፃናትና አዋቂዎች ውድድር መካሄዱን ጠቁመዋል።

በ21 ኪሎ ሜትር ውድድር በወንዶች አንድ ሰዓት ከአንድ ደቂቃ 52 ሴኮንድ በሆነ ጊዜ አንደኛ የወጣው አትሌት አበባው ደሴ ለኢዜአ በሰጠው አስተያየት ውድድሩ ብርቱ ፉክክር የታየበት መሆኑን ተናግሯል።

የሀዋሳ አየር ንብረት ፀባይ ለውድድሩ ምቹ እንደሆነ ጠቅሶ በከተማዋ ተመሳሳይ ውድድሮች ሊስፋፉ እንሚገባ ጠቁሟል።

በሴቶች አንድ ሰዓት ከ12 ደቂቃ ከ44 ሴኮንድ አንደኛ የወጣችው አትሌት የኔነሽ ደጀኔ ውድድሩ የመጀመሪያዋ እንደሆነ ተናግራለች።

እንዲህ አይነት ኩነት ለተተኪ አትሌቶች መፍለቅ የሚያበረክተው አስተዋፅዖ ከፍተኛ በመሆኑ በሌሎች ከተሞችም ተጠናክሮ ቢቀጥል መልካም እንደሆነ አመልክታለች።

በውድድሩበ አንደኝነት ላጠናቀቁ ለእያንዳንዳቸው 50 ሺህ ብር እንዲሁም በወንዶች ከአንድ ሰዓት በፊት በሴቶች ደግሞ ከ70 ደቂቃ በፊት ውድድሩን ለሚያጠናቅቁ አትሌቶች ለእያንዳንዳቸው የ100 ሺህ ብር ተጨማሪ ሽልማት ተዘጋጅቶ እንደነበርም ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም