የነፃነት ቀንዲል ነጸብራቅ የአንድነት ተምሳሌት-አድዋ! - ኢዜአ አማርኛ
የነፃነት ቀንዲል ነጸብራቅ የአንድነት ተምሳሌት-አድዋ!

በእንግዳው ከፍያለው (ኢዜአ)
አድዋን ስናስብ ከኢትዮጵያ አራቱም ማዕዘናት የተሰባሰበው ጦር ወደ ሰሜን የሀገሪቱ ክፍል ተሞ ለወረራ የመጣውን ፋሺስት ጣሊያንን ድል የነሳባት ቦታ ብቻ አድርገን የምናያት አይደለችም። ወራሪው ኃይል በጀግኖች አባቶቻችን አከርካሪው ተመቶ ሽንፈት የተከናነበባት ምደር ናት ብቻ ማለትም በቂ አይሆንም፤ በእብሪት ተወጥረው የነበሩ ነጭ ቅኝ ገዥዎች ድንገት የተነፈሱበት ቦታ ብቻ አድርገን ከደምደምንም ድሉን ማሳነስ ይሆናል። ታዲያ ምን እንበላት አድዋን? የሚል ጥያቄ ሊመጣባችሁ ይችላል። በመላው የጥቁር ህዝብና በቅኝ ግዛት ባርነት ውስጥ ወድቀው በነበሩ የተገፉ ህዝቦች ልብ የታተመች፣ ለእነዚህ ህዝቦችም የነፃነት ቀንዲልን ያጎናጸፈች የዓርነት ምልክት ጭምር ናት-አድዋ!።
የአድዋ ድል በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በቅኝ ግዛት አስተዳደር ስር ወድቀው በነበሩ የላቲንና የእስያ አገራት የነፃነት ተጋድሎ እንዲቀጣጠል ምክንያት ሆኗል። የተገፉ ህዝቦች የነፃነት መለያ ምልክት ሆኖ ሲዘከር ኖሯል፣ ዛሬም ወደፊትም መዘከሩ ይቀጥላል።
እኤአ በ1885 ጀርመን አገር በተካሄደው የበርሊን ኮንፈረንስ አውሮፓውያን መላ አፍሪካን በካርታ ላይ የተከፋፈሉትን በተግባር መሬት ላይ ለመቀራመት ጦራቸውን ሰብቀው፣ ስንቃቸውን ጭነውና ትጥቃቸውን አጥብቀው ያካሄዱት ዘመቻና የወረራ ጉዞ የተገታባት አድዋ እና እለቷ ዛሬ ድረስ በተገፉ ህዝቦች ልብ ታትማ በአዕምሮ ውስጥ ተቀርጻ ትኖራለች። ጣሊያን የኢትዮጵያን መሬት፣ የአየር ንብረትና መልክዓ ምድር ተቆጣጥሮ ሀብቷን ለሮምና ለመላው አውሮፓ ለማቅረብ የቋመጠበት የዘመናት ህልሙ የተኮላሸበት ቦታ ጭምር ናት - አድዋ።
ይህ ወራሪ ኃይል ሊቢያን በእጁ ካስገባ በኋላ ጉዞውን በቀይ ባሕር አስመራ አድርጎ መላ ኢትዮጵያን የመቆጣጠር ግብ ነበረው። ጄነራል ባራቴሪ የመደባቸው ጄነራል አልበርቶኒ፣ ጄኔራል አሪሞንዲ እና ጄነራል ቦርሜዳ በግንባር የተሰለፈውን ጦር ሲመሩ የኋላ ደጀንም እንደነበራቸው የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። ከ17 ሺህ በላይ የጣሊያን ሠራዊት 66 የሚሆኑ መድፎች፣ በርካታ መትረየሶች እና አውቶማቲክ መሳሪያዎችን ታጥቆ የግንባር ሜዳው ላይ ስለመድረሱ "የኢትዮጵያ ታሪክ ከመጀመሪያው እስካሁኑ ዘመን" በሚል በአንድርዜይ ባርይትኒስኪ እና ዮዓና ማንቴል-ኒየችኮ ተጽፎ በዓለማየሁ አበበ የተተረጎመው መጽሐፍ ያስረዳል።
በአንጻሩ ዓጼ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ ከሚመሩት ጦር በተጨማሪ በፊታውራሪ ገበየሁ፣ ንጉስ ተክለ ሃይማኖት፣ ራስ ወሌ፣ ራስ ሚካኤል፣ ራስ መኮንን፣ ዋግሹም ጓንጉል እንዲሁም ከትግራይ ገዢዎች በራስ መንገሻ፣ ራስ አሉላና ሐጎስ የሚመራ በአጠቃላይ ከ73 ሺህ እስከ 100 ሺህ የሚገመት ጦር በግንባር መሰለፉን መጽሐፉ አትቷል። መጽሐፉ እንደሚያስረዳው የራስ መኮንን ጦር ቀድሞ አምባለጌ ደርሶ በአካባቢው መሽጎ የነበረውን የጣሊያን ጦር ደምስሶ መቐለን ማስለቀቁ የኢትዮጵያ ጦር የሞራል የበላይነት ይዞ ወደ አድዋ እንዲዘምት አድርጎታል። በአምባላጌ የተሸነፈው የጣሊያን ጦር በበኩሉ የደረሰበትን የሞራል ልሽቀት ለመመለስ ፊቱን ወደ አድዋ አዙሯል።
የዛሬ የ127 ዓመት፤ ዕለቱም የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም በአድዋ ጦርነት ዓለም የተደመመበትና ዛሬ ድረስ እንቆቅልሽ የሆነበት ደማቅ ታሪክ በጀግኖች አባቶች ተሰራ። ከንጋቱ 11:00 ሰዓት አካባቢ የዓጼ ምኒልክ ጦር በስንቅ እጥረትና በሌሎች ምክንያቶች ተበትኗል በሚል የመጣው የጣሊያን ጦር በቀላሉ አድዋን ተቆጣጠሮ ወደ ፊት ለመግፋት ጦርነቱን ስለመጀመሩ በታሪክ ድርሳናት ተቀምጧል። በወቅቱ ለጣሊያን የተሳሳተ መረጃ በመስጠት የጣሊያን ጦር መሃል እንዲገባ ያደረጉ እንደ በሻህ አውአሎም ያሉ ጀግኖች የተወጡት ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
በሶሎዳ፣ ማርያም ሸዊቶ፣ አዲ ተቡን፣ ረቢ አርእየኒ በሚባሉና ሌሎች የአድዋ ተራሮች ላይ የመሸገው የኢትዮጵያ ጦርም መሃል የገባውን ጠላት እንደ በጋ ስንዴ እያጨደ መሬት ላይ እንዳሰጣው ታሪክ መስክር ነው። የጣሊያን መንግስት ለብዙ ጊዜ የተዘጋጀበት ጦርነት በአምስት ሰዓታት ጊዜ ውስጥ ተደመደመ። ጀግኖች አባቶች ዓለምን ያስደመመ ደማቅ ድል በደምና አጥንታቸው ጻፉ። ድሉም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ነፃነት ከማስከበር አልፎ ለመላው ጥቁር ህዝብና በቅኝ ግዛት ባርነት ውስጥ የነበሩ የእስያና ላቲን አገራት ለነፃነታቸው እንዲታገሉ ትልቅ የሞራል ስንቅ ሆነ።
በጦርነቱ የጣሊያን መንግስት የጎመጀውን የኢትዮጵያን መሬት ሊያገኝ ይቅርና ከ11 ሺህ በላይ ሠራዊቱ ሙትና ቁስለኛ ሆኑ። 4ሺህ የሚሆኑት ደግሞ ለጀግኖች አባቶቻችን እጃቸውን ሰጥተው ተማረኩ። እንዲሁም 56 መድፎች፣ በርካታ መትረየሶች እና ሌሎች አውቶማቲክ መሳሪያዎቹን ለወገን ጦር አስረከበ። በአድዋ ድል ከሮም እስከ አስመራ እንደ ፊኛ የተወጠረው እብሪቱ ፈንድቶ መላ አውሮፓ በሃፍረት ራደ። የቀረው የፋሽስት ሠራዊትም ተንጠባጥቦ እግሬ አውጪኝ ብሎ ፈረጠጠ። ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ክብር፣ ነፃነትና ሉዓላዊነት በአውደ ግንባሩ በፈጸሙት የጀግንነት ተጋድሎ ዓለምን ያስደመመና መላውን ጥቁር ሕዝብ ያኮራ ድል ተጎናጽፈዋል። በወቅቱ ነጭን ታግሎ ማሸነፍ አይቻልም የሚለውን አስተሳሰብ በይቻላል ተክቶ ሌሎችም ለነፃነታቸው እንዲታገሉ ያነሳሳ ደማቅ የታሪክ አሻራ አኑረዋል።
የአድዋን ጦርነት የተለየ ከሚያደርጉት ጉዳዮች አንዱ ጦርነቱ ከመጀመሩ አስቀድሞ ሁለቱም ወገኖች አሸናፊ ለመሆን የተለያዩ ስልቶችን መጠቀማቸው ነው። ጀኔራል ባራቴሪ ባይሳካለትም ቅሉ የትግራዩን ገዥ ራስ መንገሻን ጨምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የየአካባቢውን ገዥዎች ዳግማዊ አፄ ምኒልክን ክደው ጣሊያንን እንዲተባበሩ ለማድረግ መሳሪያ በመስጠት፣ የተለያዩ ስጦታዎችን በማቅረብና "ስልጣን እንሰጣችኋለን" በማለት የመከፋፈል ሥራ በስፋት ለመስራት ሞክሯል። በተጨማሪም ዓፄ ምኒልክን አታሎ ስምምነት እንዲፈርምና ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ከጎኑ ለማሰለፍ ያደረገው ጥረት በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ለእዚህም ለጦርነቱ ምክንያት የሆነውን የውጫሌ ውል አንቀጽ 17 በማሳያነት መጥቀስ ይቻላል።
በዓፄ ምኒልክ በኩልም ከጣሊያን ጋር በድብቅ ስምምነት የሚፈጽሙ የአካባቢ ገዥዎችን በምህረት በመመለስ ከጎናቸው አሰልፈዋል። እምቢ ያሉትን በመቅጣት፣ ከውጭ ሀገራት ጋርም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በመፍጠርና በማግባባት ጭምር የነፍስ ወከፍ ጦር መሳሪያ ከፈረንሳይና ከሌሎች አገራት አስገብተዋል። ከአልበርቶኒ ጋር የሚስማሙ መስለው ጊዜ በመግዛት ለማይቀረው ጦርነት ያደረጉት ዝግጅት እንደዋዛ አይታይም። ኋላም በጦርነቱ የተገኘው ድል ሲታይም ፃጼ ምኒልክ ከጄኔራሉ የበለጠ ስልታዊ መሪ አስብሏቸዋል።
በጦርነቱ በቴክኖሎጂ፣ በዘመነ ሠራዊት፣ በስንቅና ትጥቅ አቅርቦት እንዲሁም ከአሰላለፍ አንጻር በጣሊያንና በኢትዮጵያ መካከል የነበረው ልዩነት የምድርና የሰማይ ያህል የሚራራቅ ነው። በአድዋ ጦርነት የኢትዮጵያ ጦር ይዞ የተሰለፈው መሳሪያ፣ ጦርና ጋሻ ከዘመኑ ስልጣኔ አንጻር ሲታይ እጅግ ኋላ ቀር ቢሆንም ጀግኖች አባቶቻችን በአድዋ ተራሮች ላይ በከፈሉት የጀግንነት ተጓድሎ የጣሊያንን ወራሪ ጦር ድል በማድረግ ዓለምን በእጅጉ ያስደመመ ለመላው ጥቁር ህዝቦች የነፃነት ብስራትን በየካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም በአድዋ ተራሮች አብስረዋል።
በአድዋ ድል የነገሱ ጀግኖች አባቶቻችን የድል ሚስጢር ምንድን ነው? የሚለው በቀዳሚነት መታየት ያለበት ጉዳይ ይመስለኛል። የአሁኑ ትውልድ ከጀግኖች አባቶች ምን ትምህርት መውሰድ አለበት? አሁን ሀገር እየገጠሟት ያሉ ችግሮችን በፅናት በማለፍ እንዴት ኢትዮጵያን ማሳደግና ማጽናት ይቻላል? የሚለው ላይ ትውልድ መግባባት ያስፈልገዋል።
ጀግኖች አባቶቻችን የአድዋን ጦርነት በድል ያጠናቀቁበት አንዱ ስልት የፋሺስት ጣሊያንን የመከፋፈል ሴራ በመበጣጠስ ነው። ከምስራቅ እስከ ምዕራብ፤ ከደቡብ እስከ ሰሜን ኢትዮጵያዊያን የዳግማዊ ዓፄ ምኒልክን የሀገር ጥሪ ተቀብለው በአንድነትና በህብረት ወደ አውደ ግንባር መትመማቸውም ዋነኛ የድሉ ምስጢር ነው። ከንጉሱ ጋር የሃሳብ ልዩነት ያላቸው መኳንንቶች፣ የጎበዝ አለቆች እና ዱር ቤቴ ብለው የሸፈቱ አርበኞች ሳይቀሩ በአድዋ ጦርነት ልዩነታቸውን ወደ ጎን ብለው አብሮነታቸውን አሳይተዋል።
የንጉሱን "ሃገርና ሃይማኖት የሚያጠፋ ጠላት ባህር ተሻግሮ…ያገሬ ሰው ጉልበት ያለህ ተከተለኝ፣ ጉልበት የሌለህ በጸሎት እርዳኝ" የሚለውን አዋጅ ኢትዮጵያዊያን ሲሰሙ በአንድነት ወደ አድዋ በመትመም በሀገራቸው ጉዳይ ልዩነት እንደሌላቸው አሳይተዋል። በጦር ግንባርም በጋራ በመዋጋት በአንድነት ሞተውና ቆስለው ሕብረታቸውን አስመስክረዋል። የአድዋ ድል ኢትዮጵያዊያን በጽናትና በአንድነት ያመጡት ድል መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። አንዱ ጠላትን በግንባር ሲፋለም ሌላው ስንቅ አዘጋጅቶ አቅብሏል፣ በኋላ ደጀን የወገንን ጦር በማበርታትና ምርኮኛን በማንሳት ጭምር የበኩሉን ተወጥቷል።
የአሁኑ ትውልድ ከጀግኖች አባቶቻችን መውረስ ያለበት ይሄን የአገርና የህዝብ ፍቅር፣ የዓላማ ጽናት እንዲሁም ቁርጠኝነትና አንድነትን ነው። ከምንም በላይ አሁን እየገጠሙን ላሉ የጣሊያን ፋሽስት የመከፋፈል ቅሪት ሳንካዎችን መፍቻ ቁልፉ አብሮነት መሆኑን መረዳት ይገባል። ከመረዳት ባለፈም ጉልበት ያለው ለፍቅር፣ ለአንድነት፣ ለአብሮነትና ለአገር ግንባታ የሚሰራውን ይከተል። አቅመ ደካማው ደግሞ በጸሎቱ ይርዳ። በአንድነት ለመጽናት "የእናቴ ቀሚስ አደናቀፈኝ" የሚባለውን አይነት ሰበብ ወደ ጎን ማለት ያስፈልጋል። ከወንዜና ከመንደር አስተሳሰብና አመለካከት ወጥቶ ታላቋን ኢትዮጵያ ከፍ ለማድረግ በዓላማ ጽናትና በቁርጠኝነት መስራትም ያስፈልጋል።
እርግጥ ነው ይህ ትውልድ ዘመኑ የሚጠይቀውን ጀግንነት በልማት፣ በአገር እድገትና ሉዓላዊነት በማስከበር እየደገመው ነው። ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የዛሬው ትውልድ አንዱ የጀግንነት አርማ ሆኖ በታሪክ ሲታወስ ይኖራል። ሠራተኛው ከደመወዙ፣ ገበሬው ከምርቱ፣ ነጋዴው ከትርፉ፣ ጉሊት ቸርቻሪዋ ከመቀነቷ አውጥተው የገነቡት ነው። ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለግድቡ የበኩሉን አድርጎ አሻራውን አሳርፏል፤ እያሳረፈም ይገኛል። መላው ኢትዮጵያዊያን በሀሳብ፣ በጉልበት፣ በገንዘብ አስተዋጽኦ በማድረግ ግድቡ አሁን የደረሰበት ደረጃ ላይ ደርሷል። በቀጣይም የዛሬው ትውልድ በመንግስት የሚቀረጹ የልማት ፕሮጀክቶችን አውን በማድረግ የራሱን ደማቅ ታሪክ እንደሚጽፍ ማረጋገጫ ነው።
የዛሬው ትውልድ የጥንት አባቶቹን ፈለግ ተከትሎ ኢትዮጵያ ጸንታ እንድትቆይና ሁሌም ሉዓላዊነቷ እንዲጠበቅ ከሁሉም በላይ አንድነቱን ማጠንከር ይኖረበታል። ድር ቢያብር አንበሳ ያስር እንደሚባለው ከእኔነት አስተሳሰብ ወጥቶ በአብሮነት ላይ ከእዚህ ከፍ ሲልም እንደሀገር አስቦ መንቀሳቀስ ይኖርበታል።
ጀግኖች አባቶቻችን በዚያን ወቅት በታጠቀው ዘመናዊ መሳሪያ ለመድፈር ይቅርና ሊታሰብ የማይችል የሚመስለውን ወራሪው የጣሊያን ጦርን ድል የነሱት የውስጥ ልዩነትን ትተው አንድ በመሆናቸው ነው። ዛሬም ጠፍሮ የያዘንን ድህነት ድል በመንሳት ሀገርን ወደ ብልፅግና ማማ ማምጣትና ዜጎችን ተጠቃሚና የተሻለች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እርስ በርስ መከፋፈልን መተው ያስፈልጋል። የእኛ የምንለውን ጎጥና መንደር ሳይሆን ትልቁን የኢትዮጵዊነትን ምስል ማሰብ ነው የሚበጀው። ያኔ ለእኔ የሚለው ቀርቶ ለእኛ ማለት እንጀምራለን። እንዲህ አብሮነቱ ሲጸናና ሲጠናክር ደግሞ ጥንታዊ፤ ታሪካዊቷና የነፃነት ቀንዲልና ተምሳሌት የሆነችው ኢትዮጵያችን ታፍራና ተከብራ ትኖራለች።