ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፎች የሰጠችው ትኩረት ለምስራቅ አፍሪካ አገራት አብነት የሚሆን ነው-የኡጋንዳ ፓርላማ አባላት

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 19/2015 ኢትዮጵያ ለሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፎች የሰጠችው ትኩረት ለምስራቅ አፍሪካ አገራት አብነት የሚሆን ነው ሲሉ የኡጋንዳ ፓርላማ አባላት ተናገሩ፡፡

ኢትዮጵያ ለዘርፎቹ ግልጽ ፖሊሲ በማስቀመጥና የተጠናከረ ተቋማዊ አደረጃጀት በመፍጠር ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡

የኡጋንዳ ፓርላማ አባላት ልዑክ በኢትዮጵያ የአምስት ቀናት ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፤ በጉብኝታቸውም በኢትዮጵያ ያሉ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ተቋማትን የስራ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል፡፡ 

የልዑኩ አባላት በዚሁ ጊዜ ኢትዮጵያ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ እየተከተለች ያለው ፖሊሲና ህጋዊ አሰራሮች ዘርፉን ለማሳደግ መሰረት የሚጥሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ 

የልዑክ ቡድኑን የመሩት ፍሎረንስ አኪኪ የኢትዮጵያ መንግስት ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽንን የአገሪቷ እድገትን ለመምራት ቁልፍ ጉዳይ አድርገው እየሰሩበት መሆኑን እንደተገነዘቡ ይናገራሉ፡፡ 

ኢትዮጵያ የሳተላይት መረጃ መቀበያና መቆጣጠሪያ ማዕከል በመገንባት ጭምር እየሰራች መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ኢትዮጵያ በአህጉሪቷ የቴክኖሎጂ ዘርፍ እሄደችበት ያለውን መንገድ እንደሚያሳይ አንስተዋል፡፡ 

የእንጦጦ ኦብዞርቫቶሪ ምርምር ማዕከል አሁን ላይ ለተለያዩ ጉዳዮች የሚያገለግሉ የሳተላይት መረጃዎችን በመቀበል እየሰራ መሆኑን ለአብነት በመጥቀስ፡፡ 

ከዚህ አኳያ በኡጋንዳ ያሉ የዘርፉ ባለሙያዎች ከኢትዮጵያ አቻዎቻቸው ጋር ተቀራርበው እንዲሰሩ እንሻለን ነው ያሉት፡፡ 

አፍሪካ በተለይ በህዋ ሳይንስ ምርምር ዘርፍ በቂ ስራ እያከናወነች አለመሆኑንም ነው የረተናገሩት፡፡ 

ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ መንግስት ሃብት በመመደብ ጭምር ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት የሚደነቅ መሆኑን አንስተው፤ ይህም ከኢትዮጵያ ባሻገር በመላው አፍሪካ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ መሆኑን አብራርተዋል፡፡  

ሌላኛው የልዑክ ቡድኑ አባል በርናርድ ኦድዌ ሙቱሳ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሻለ ስራ እያከናወነች ስለመሆኑ አንስተዋል፡፡ 

ኢትዮጵያ በዘርፉ የሰው ሃብት በማፍራትና የመሰረተ ልማትን በማስፋፋት ረገድ የተሻለ ስራ ስለማከናወኗ አንስተው፤ ይህም በተለይ የቀጠናው አገራት ከኢትዮጵያ ጋር በዘርፉ ተቀራርበው እንዲሰሩ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን አብራርተዋል፡፡  

በጉብኝታቸው ኢትዮጵያ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍን በተሻለ ተቋማዊ አደረጃጀት እየመራች መሆኑን እንደተገነዘቡ የተናገሩት ደግሞ ሌላኛዋ የልዑክ ቡድኑ አባል ቤቲ ኦውል ናቸው፡፡ 

ተቋማዊ አደረጃጀቶች በተሻለ መልኩ ተናበውና ተቀናጅተው እየሰሩ ስለመሆኑ መገንዘባቸውንም ነው የገለጹት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም