ቀጥታ፡

አድዋ በሠዓሊያን ዐይን

ሥነ-ጥበብ ብዙ ዓይነት የሰው ልጅ ድርጊቶችን ያጠቃልላል።

ከነዚህም የሥነ-ጥበብ ዘርፎች አንዱ ስነ-ሥዕል ሲሆን በአንድ የሥዕል ጥበብ የተወሰነ ርዕሰ ጉዳይን ወይም በርካታ ሀሳብን መግለፅ ይቻላል።

በሥዕል ጥበብ ከተገለፁት የኢትዮጵያ ታሪክ ክንውኖች መካከል ደግሞ የአድዋ ጦርነት አንዱ ሲሆን በርካታ ኢትዮጵያውያን ሠዓሊዎች አድዋን በተመለከተ የሥዕል ሥራዎቻቸውን በተለያዩ ጊዜያት አቅርበዋል።

ከእነዚህም መካከል በ1988ዓ.ም የአድዋ ድል 100ኛ ዓመት ሲከበር በሠዓሊ እሸቱ ጥሩነህ የተሳለው "የአሸናፊው ምኅረት" ወይም "magnanimity of the victor" በሚል ርዕስ የቀረበው ሥዕል ይጠቀሳል።

ሠዓሊው ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ባደረገው ቆይታ በጦርነቱ ለተማረኩ የጣሊያን ወታደሮች የተደረገላቸውን ምህረት መነሻ በማድረግ ሥዕሉን መሥራቱን ገልጿል።

በተለይም አጼ ምኒሊክ በአድዋ ጦርነት ወቅት የተማረከን የጣሊያን ጄነራል የክብር ሻሞላ ወደ ቤተሰቦቹ የላኩበት የታሪክ ሂደት የሥዕሉ መነሻ ሀሳብ እንደሆነ ተናግሯል።

በመሆኑም አድዋ የጥቁር ሕዝቦች ድል ከመሆኑ ባሻገር የምህረትና ይቅርታ ማሳያ በመሆን ትልቅ መልዕክት እንደሚያስተላልፍ ተናግረዋል፡፡

"የታሪክ ቅብብሎሽ" እና "የድል ብሥራት" በሚል አድዋን የተመለከቱ ሥዕሎች የሳለችው የኅብር የሠዓሊያን ቡድን አባልና የሙሉ ጊዜ ሠዓሊ ብርቱካን ደጀኔ "አድዋ የጥቁር ህዝቦች ነፃነትና የአንድነት ምሳሌ ነው" ትላለች።

አድዋ በታሪክ ቅብብሎሽ በሀገር ጉዳይ አንድ መሆን የምንማርበት የኢትዮጵያውያን የጋራ ድል መሆኑን ሠዓሊ ብርቱካን ታስረዳለች።

የአድዋ ድል የሴቶችን ብልሃትና ትልቅ አቅም ያሳየ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ "አድዋና ጣይቱ" በሚል የሥዕል ሥራውን ያቀረበው ሠዓሊ ካሌብ ብርሃኑ ነው።

በአድዋ ጦርነት ኢትዮጵያውያን ከአራቱም ማዕዘን በመሰባሰብ የአገራቸውን ዳር ድንበር ሊደፍር የመጣን የጣሊያን ወራሪ ኃይል በማሸነፍ ዓለምን ያስደነቀ የጥቁር ህዝብ የድል ታሪክ ፅፈዋል፤ በዚህም የነጭ የበላይነት አስተሳሰብን በመስበር የሰው ልጅ እኩልነትን አብስረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም