የሸገር ከተማ አገልግሎትን ለማዘመን ታልሞ የተመሰረተ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የሸገር ከተማ አገልግሎትን ለማዘመን ታልሞ የተመሰረተ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ

የካቲት 19 ቀን 2015 (ኢዜአ) የሸገር ከተማ የህዝብን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አገልግሎት ለማዘመን ታልሞ የተመሰረተ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።
የሸገር ከተማ ምስረታ ይፋዊ የማብሰሪያ መርሃ-ግብር በሸገር ከተማ ዋናው መስሪያ ቤት ተካሂዷል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የክልሉ ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ፤ ዘመኑን ያማከሉ፣ ለህዝብ የቀረቡና የዲጂታል አገልግሎት የሚሰጡ ከተሞችን መመስረት ጊዜው የሚፈልገው ጉዳይ ነው።
የሸገር ከተማ አርሶ አደሩን ወደ ዘመናዊ ግብርና በማምጣት ከራሱ አልፎ ለመላው ኢትዮጵያ የሚተርፍ ምርት እንዲያመርት ለማስቻል እንደሆነ ተናግረዋል።
በመሆኑም ሸገር በብዙ ጥናትና ምክክር የተመሰረተ ከተማ መሆኑን ጠቅሰው፤ ህዝቡን ለዘመነ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አገልግሎት ለማብቃት ታልሞ የተመሰረተ መሆኑንም ተናግረዋል።
ሸገር በርካታ ዓላማዎችን ሰንቆ የተመሰረተ ከተማ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የሸገር ከተማ ከንቲባ ዶክተር ተሾመ አዱኛ ናቸው።
የከተማ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ የስራ እድል መፍጠር፣ ጠንካራ ከተማና ዘመናዊ የከተማ መሰረተ ልማት መገንባት፣ የከተማ ግብርናን ማዘመን እና ዲጂታላይዝ የሆነ የከተማ ማህበራዊ አገልግሎትን ማዘመን ከተማው የተመሰረተባቸው ዋነኞቹ ዓላማዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
የኦሮሚያ ክልል የቀድሞ ፕሬዝዳንት አቶ አባዱላ ገመዳ በበኩላቸው ዘመናዊ ከተሞችን መመስረት ለክልሉም ሆነ ለኢትዮጵያ እድገት ወሳኝ ነው ብለዋል።

ትልቁ አጀንዳችን ከድህነት መውጣት ነው ያሉት አቶ አባዱላ፤ ይህንን ማድረግ የሚቻለውም ሸገርን የመሳሰሉ ዘመናዊ ከተሞችን በመመስረትና ተግቶ በመስራት እንደሆነ አስገንዝበዋል።
በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉትን ከተሞችና የገጠር ቀበሌዎችን አንድ ላይ በማሰባሰብ የተመሰረተው ሸገር ከተማ 12 ክፍለ ከተማና 36 ወረዳዎችን በማቀፍ የተመሰረተ ነው።

በፓናል ውይይት፣ የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ፣ የፈረሰኞች ትርኢት እና ሌሎች መርሃግብሮች ሲካሄድ የነበረው የሸገር ከተማ ምስረታ መርሃ ግብር ዛሬ በዋናው መስሪያ ቤቱ በተከናወኑ ይፋዊ የማብሰሪያ መርሃግብሮች ተካሂዷል።