ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የወተት ምርታማነትን ለማሳደግ የዝርያ ማሻሻያ ማዕከላትን በማጠናከር ገበያ ተኮር የአመራረት ዘዴን መከተል ይገባል

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 19/2015 በኢትዮጵያ የወተት ምርታማነትን ለማሳደግ የዝርያ ማሻሻያ ማዕከላትን በማጠናከር ገበያ ተኮር የአመራረት ዘዴን መከተል እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡

ኢትዮጵያ በእንሳሳት ሀብት በአፍሪካ ቀዳሚ የሚባል ቦታ ቢኖራትም የሚጠበቀውን ያህል ውጤት እያገኘች አለመሆኑ የአደባባይ ሀቅ ነው።      

እንደ ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኮሚሽን መረጃ የኢትዮጵያ አጠቃላይ ዓመታዊ የወተት ምርት ከ7 ነጥብ 1 ቢሊዮን ሊትር የማይበልጥ ሲሆን፤ የነፍስ ወከፍ ፍጆታም ከ66 ሊትር አይበልጥም፡፡

ይህም አንድ ጤነኛ ሰው በዓመት ከሚያስፈልገው 200 ሊትር አንጻር አነስተኛ መጠን ነው፡፡

ለ27 ዓመታት የወተት ልማት ባለሙያ ሆነው ያገለገሉትና በአሁኑ ወቅት ኤስ አንድ ቪ በተሰኘው የኔዘርላንድ የልማት ድርጅት ውስጥ በአማካሪነት የሚሰሩት አቶ አዳነ ኪታባ በዚህ ሀሳብ ይስማማሉ።

የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣የከተሜነት ማደግና ኢንዱስትሪዎች መስፋፋትን የሚመጥን የወተት ምርት ሊኖር እንደሚገባ የሚናገሩት ባለሙያው አሁን ባለው አካሔድ ፍላጎቱን ማሳካት እንደማይቻል ይጠቅሳሉ ።  

ለዚህ ደግሞ አንዱ መፍትሄ ገበያ ተኮር የአመራረት ዘዴን መከተል ተገቢና አዋጭ መሆኑን ይመክራሉ። 

በአሁን ወቅት የወተት ምርት እየሰጡ ያሉት ፎገራ፣ ቦረና ፣ አርሲ ፣ከረዩና ሱማሌ ዝርያዎች ሲሆን ምርታማነታቸው በቂ ባለመሆኑ የዝርያ ማሻሻያ ሥራዎችን መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።   

ለዚህ ውጤታማነት ደግሞ የዝርያ ማሻሻያ ማዕከላትን ማጠናከርና ያላቸውን አቅም አሟጠው እንዲጠቀሙ ማድረግ ተገቢ መሆኑንም ጠቅሰዋል።  

በአሁኑ ወቅት የከብቶች ዝርያን የማሻሻል ስራ ወጥ በሆነ መንገድ አለመተግበሩ በዘርፉ ትልቅ ተግዳሮት መሆኑንም ጭምር ነው የሚያብራሩት።

ባለሙያው እንደሚሉት፤ለወተት ምርታማነት መጨመር በቂ የመኖ አቅርቦት መኖርም አንዱና ወሳኝ በመሆኑ ከዚህ አኳያ የሚታዩ ችግሮችን ማቃለል ይገባል ይላሉ።  

የሕዝብ ቁጥር መጨመር እና የእርሻ ስራ መስፋፋት የግጦሽ መሬት እንዲያንስ ከማድረጉ ባሻገር የመኖ አቅርቦት በበቂ መጠን እንዳይኖር ያደረገ ሌላው ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።

መንግሥት ከሚያቀርበው የተሻሻለ መኖ በተጓዳኝ የግል ዘርፉ  በስፋት ሊሰማራበት የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋትም እንዲሁ ቁልፍ ጉዳይ እንደሆነ አንስተዋል።  

ገበያው ላይ ለወተት ዋጋ መጨመር አንዱ ምክንያት የመኖ አቅርቦት እጥረት እንደሆነ አንስተው እንደ በቆሎና አልፋ የተሰኙ መኖዎችን የማምረት ስራ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።  

በተጨማሪም በኢትዮጵያ ዝናብ ባለበት ወቅት የሚተርፈውን መኖ አስቀምጦ እጥረት በሚያጋጥምበት ወቅት መጠቀም ላይ ክፍተት መኖሩን ያመለከቱት ባለሙያው በዚህ መስክም ሊሰራ እንደሚገባ እንዲሁ።

ከወተት ምርት ሰንሰለቱ ጋር በተያያዘ በምርት ወቅት ፣ ሲሰበሰብና ሲከፋፈል ትክክለኛውን እሴት ሰንሰለት የጠበቀና በቴክኖሎጂ የታገዘ መሆኑን ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል።  

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከ40 በላይ ወተት የሚያቀናብሩ ኢንዱስትሪዎች አሉ ያሉት አቶ አዳነ ኢንዱስትሪዎችም ወተት አምራቹን መደገፍ አለባቸው ብለዋል።  

በተለይ አምራቾቹ ያሉባቸው የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ክፍተቶች እንዲሞሉ ኢንዱስትሪዎች የድርቸውን መወጣት እንደሚኖርባቸውም ነው ያመለከቱት።   

የወተት ምርታማነት ከጥራት ጋር ካልተሰናሰለ ትርጉም እንደሌለው የገለጹት አቶ አዳነ የወተት ምርት ጥራት የመፍትሄ እርምጃዎች ሊወሰዱ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም