ባለፉት ሰባት ወራት ከ236 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል- የገቢዎች ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት ሰባት ወራት ከ236 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል- የገቢዎች ሚኒስቴር
ሐዋሳ(ኢዜአ) የካቲት 18/2015 በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት ሰባት ወራት ከ236 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የገቢዎች ሚኒስትሯ አይናለም ንጉሴ አስታወቁ ፡፡
ቀልጣፋ የታክስ ስርዓት ለመገንባት በኤሌክትሮኒክ-ታክስ ስርዓት ግብርን አሳውቆ ለመክፈል የሚያስችሉ ስራዎች መሰራታቸውንና በርካታ ግብር ከፋዮች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በጉምሩክ ኮሚሽንም የጉምሩክ አገልግሎቱን ወረቀት አልባ በማድረግ ተቋማዊ የአሰራር ልህቀት የማረጋገጥ ስራ መከነወኑን ተናግረዋል፡፡
በሰባት ወራት ከተስተናገዱ 78 ሺህ 277 ሰነዶች ውስጥ የማዋል ጣልቃ ገብነቱ 2 ሺህ 997 ብቻ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የገቢ እቅዱን ለማሳካት ግብር ከፋዮችንና ባለድርሻ አካላትን ማወያየት፣ ብልሹ አሰራሮችን ማስተካከልና እርምጃ መውሰድና በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ችግሮችን በመቅረፍ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡
የግብር ስወራና ማጭበርበር፣ ህገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድን ጨምሮ በህግ ተገዥነት ላይ ያለውን ውስንነት በእቅድ አፈጻሙ በተግዳሮት ተነስቷል፡፡
የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቀበታ በበኩላቸው የበጀት ዓመቱ ገቢ አሰባሰብ ትልቅ ግብ የተጣለበትና የተገኘው ውጤትም አመርቂ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ውጤቱ በቅንጅት በመመራቱ የተገኙ መሆኑን ጠቅሰው በገቢዎች ሚኒስቴርም ሆነ በጉምሩክ ኮሚሽን የተሰሩ የአሰራርና የህግ ማእቀፎችና የአገልግሎት ደንቦች ተገልጋይ ተኮር ሆኖ መሻሻላቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ገቢ ከመሰብሰብ ባለፈ በየዘርፉ የሚሰጡ አገልግሎቶች የተገልጋዩን ፍላጎት የሚያሳኩ እንዲሆኑ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ በቴክኖሎጂ የታገዙ ስራዎች ለተገኘው ውጤት ከፍተኛ ድርሻ አላቸው ብለዋል፡፡
በኢንደስትሪ ፓርኮች በሚሰጠው አገልግሎት ላይ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በመድረኩ የተሳተፉት በጉምሩክ ኮሚሽን የሃዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ታደሰ መርዕድ ናቸው፡፡
ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ በሀዋሳና ይርጋለም ኢንደስትሪ ፓርኮች በጨርቃጨርቅና በግብርና ምርቶች ላይ በሚደረገው የወጪ ንግድ አገልግሎት ዘርፍ ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
ባለፉት ሰባት ወራት በቅንርጫፍ ጽህፈት ቤቱ ስር በሚገኙ ሰባት ጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች ኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከል በተሰራው ስራ ከ400 ሚሊየን ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸውን እቃዎች መያዛቸውን ተናግረዋል፡፡
አዳዲስ እቃዎች፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ልባሽ ጨርቆች፣ መድሃኒቶችና የግብርና ምርቶች በኮንትሮባንድ ከተያዙት ውስጥ እንደሚገኙም ገልጸዋል፡፡
በመድረኩ ባለፈው ሰባት ወራት የተከናወኑ ተግባራትን የያዘ ሰነድ ቀርቦ ውይይት እየተደረገ የሚገኝ ሲሆን የቀጣይ የስራ ወራት አቅጣጫዎች ይቀመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡
፡የገቢዎች ሚኒስትርና የጉምሩክ ኮሚሽን ከፍተኛ አመራሮችና ከተለያዩ ተቋማት የተወከሉ ባለድርሻ አካላት በመድረኩ በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡