ቀጥታ፡

የአድዋ ድል ለብሄራዊ መግባባትና ለመከላከያ ሠራዊት ግንባታ ጉልህ አስተዋጽኦ አለው

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 18/2015፦ የአድዋን ድል ለብሄራዊ መግባባትና ለመከላከያ ሠራዊት ግንባታ እንጠቀምበታለን ሲሉ የመከላከያ ሠራዊት ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ ገለጹ።


የመከላከያ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት በ127ኛው የአደዋ ድል በዓል አከባበር በማስመልከት ከሀገር ውስጥ የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን አመራሮችና ባለሙያዎች ጋር በመከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ መምሪያ ውይይት አድርጓል።

በውይይቱ ላይ የመከላከያ ሠራዊት ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ ባስተላለፉት መልእክት መከላከያ በዓሉን በሃላፊነት ወስዶ ደረጃውን በሚመጥን መልኩ እንዲከበር ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

የአደዋ ድል የኢትዮጵያ ህዝቦች በአንድነት ሆነው በሚገባ የሰለጠነውን ወራሪ ሃይል ተዋግተው ያሸነፉት ጦርነት ነው ያሉት ጄነራሉ የዛሬ 127 ዓመት አያቶቻችን የሰለጠነና ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች የታጠቀ ሃይል እንዴት ተዋግተው እንዳሸነፉ የግንኙነት ስርዓቱ እንዴት እንደነበርና እንዴትስ ሁለገብ አመራር ሰጥተው ለድል እንደበቁ ልንማርበት ይገባል ብለዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ አክለውም የአድዋ ድል የአንድነት ተምሳሌት በመሆኑ ለብሔራዊ መግባባት ለሠራዊት ግንባታና ለቱሪዝም በመጠቀም ገጽታችንን መገንባት ይኖርብናል ሲሉም ተናግረዋል፡፡


ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካ እና የመላው ጥቁር ህዝቦች የኩራት ምንጭ የሆነውን የአድዋ ድል ታሪኩን በሚመጥን መልኩ ዘግቦ ለትውልድ ማሸጋገር ከእያንዳንዱ የመገናኛ ብዙሃን ተቋምና ባለሙያ የሚጠበቅ እንደሆነም አሳስበዋል።


የመከላከያ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ በበኩላቸው በዓሉን መከላከያ በሃላፊነት ወስዶ ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር እንዲያከብረው በመወሰኑ በተቋሙ ስም የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው የተሳካ እንዲሆንም ከመገናኛ ብዙሃን ተቋማት አመራሮችና ባለሙያዎች ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ ተሳታፊ የነበሩ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በሰጡት አስተያየት 127ኛውን የአደዋ ድል በዓል ለማክበር መከላከያ ሃላፊነት በመውሰዱ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸው በአሉ ተጀምሮ በስኬት እንዲጠናቀቅ ትኩረት ሊሰጧቸው ይገባል ያሏቸውን ሃሳቦች አንስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡


በዕለቱም ከመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ላይ የመከላከያ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ማብራርያ መስጠታቸውን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም