ቀጥታ፡

የኢትዮጵያና ሩስያ ያላቸው ታሪካዊ ግንኙነት በተለያዩ ዘርፎች እየተጠናከረ መጥቷል - አምባሳደር ኤቭጌኒ ቴርኪን

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 18/2015 ኢትዮጵያና ሩስያ ያላቸው ታሪካዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነት በተለያዩ ዘርፎች እየተጠናከረ መምጣቱን በኢትዮጵያ የሩስያ አምባሳደር ኤቭጌኒ ቴርኪን ገለጹ።

የኢትዮጵያና ሩስያ የዲፕሎማሲ ግንኙነት የጀመሩበትን 127ኛ ዓመት በዓል በአዲስ አበባ የሩስያ ኤምባሲ አክብሯል።

በኢትዮጵያ የሩስያ አምባሳደር ኤቭጌኒ ቴርኪን እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት የሩስያና ኢትዮጵያ ግንኙነት ጠንካራ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ትብብርን የበለጠ ለማጠናከር በሁለቱ አገራት ከተሞች ሞስኮና አዲስ አበባ መካከል በከፍተኛ መሪዎች ደረጃ የሚደረጉ ውይይቶችን ጠቅሰዋል።

በሁለቱ አገራት የፓርላማ ግንኙነትና በሰብዓዊ እርዳታ እንዲሁም በህዝብ ለህዝብ ያለው ግንኙነት እየተጠናከረ መምጣቱን ነው ያነሱት።

የሁለቱ አገራት ትብብር በኢንዱስትሪ፣ በግብርናና በኃይል ዘርፍም መጠናከሩን አንስተዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓና አሜሪካ ጉዳዮች ዳሬክተር ጀነራል አምባሳደር እሸቱ ጥላሁን በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ከሩስያ ጋር ጠንካራ ግንኙነት አላት።

የሁለቱ አገራት አጋርነት በተለይም በትምህርት፣ በሳይንስና በመከላከያ ዘርፍ ለማጠናከር ተጠቁሟል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ለመጣል በነበረው ስብሰባ ወቅት ሩስያ ለኢትዮጵያ ለሰጠችው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

እንደ ኤውሮፓውያን አቆጣጠር በ1896 የጣሊያንን የቅኝ ግዛት ኢትዮጵያን ለመውረር በመጣበት ጊዜ በአድዋ በተደረገው ተጋድሎ ሩስያ ከኢትዮጵያ ጎን መቆሟን አውስተዋል።

በተመሳሳይ የሶማሌ መንግሥት በ1977 በምስራቅ የአገሪቱን ክፍል ወረራ በፈጸመበት ወቅት ሩስያ የኢትዮጵያ አጋር እንደነበረችም ነው ያወሱት።

በአድዋ ጦርነት ወቅት የሩስያ ቀይ መስቀል በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ቁስለኞች የህክምና አገልግሎት በመስጠት አጋርነታቸውን እንዳሳዩ ጠቁመዋል።

በነዚህና በሌሎች በተግባር የተደገፉ ግንኙነቶች ኢትዮጵያ ከሩስያ ጋር ላላት የጠበቀ ግንኙነት ትልቅ ዋጋ እንደትሰጥ በአጽአኖት አንስተዋል።

ሩስያ በ1895 ጣሊያን ኢትዮጵያን ለመውረር በመጣችበት ወቅት 30 ሺህ ጠበንጃ 5 ሺህ ጎራዴዎችን ለኢትዮጵያ ወታደሮች መላኳን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም በጦርነቱ ወቅት ለቆሰሉና ጉዳት ለደረሰባቸውን ሰዎች የህክምና እርዳታ ለመስጠት የሩስያ ቀይ መስቀል ኢትዮጵያ መምጣቱን አስረድተዋል።

ሁለቱ አገራት ያላቸውን የጠበቀና ታሪካዊ ግንኙነት በምጣኔ ሃብት የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸው በትብብር ሊሰሩባቸው የሚችሉ በርካታ የንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዳሉ አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም