ቀጥታ፡

ዓመታዊ የቁርዓን ውድድር ዛሬ በአዲስ አባበ መካሄድ ጀመረ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 18/2015 በዘይድ ኢብን ሳቢት የቁርዓን ማኅበርና በሞሮኮው ንጉስ መሃመድ ስድስተኛ ፋውንዴሽን ድጋፍ የተዘጋጀው ዓመታዊ የቁርዓን ውድድር ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀምሯል።

በውድድሩ ከተለያዩ የአገሪቱ አከባቢዎች የተውጣጡ 50 የእምነቱ ተከታይ ወጣቶች የተሳተፉ ሲሆን ውድድሩ ዛሬ እና ነገ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ተገልጿል።

በዘይድ ኢብን ሳቢት የቁርዓን ማኅበር ፕሬዝዳንትና የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የቁርዓንና የአዛን ውድድር ዋና ኃላፊ ዶክተር ኑረዲን ቃሲም በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ በአፍሪካ 32 አገራት የሚሳተፉበት የቁርዓን ውድድር ላይ የሚሳተፉ ኢትዮጵያዊያን እየተለዩ ነው።

የቁርዓን ውድድሩ የኃይማኖትን ዕውቀት ከማሳደጉም በተጨማሪም ኢትዮጵያዊ እሴቶችን ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍና ኢትዮጵያዊያን ወጣቶችን ከሌላውን ዓለም ሕዝቦች ጋር የባህል ልውውጥ እንዲያደርጉ እድል የሚፈጠር መሆኑን ተናግረዋል።

በውድድሩ ላይ በኢትዮጵያ የሞሮኮ አምባሳደር ኑዝሓ አላዊ፣ የሠላም ሚኒስቴር ተወካይ አቶ ትዕዛዙ ደሳለኝና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተገኝቷል።

በውድድር መርኃ ግብሩ ላይ አስር አባላት ያለው የሞሮኮ ልዑክም ታድመዋል።

የተለያዩ አካላትን ያቀፈው ይኸው ልዑክ የአል ነጃሽን መስጂድ እንደሚጎበኙ የተገለጸ ሲሆን ከተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት እንደሚያደርጉም ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም