የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያከናውነውን ተግባራት አጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያከናውነውን ተግባራት አጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 18/2015 የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያከናውነውን ተግባራት አጠናክሮ እንደሚቀጥል የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደ ሃና ገለጹ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለዩኒቨርስቲው መካከለኛ አመራሮች ለዘጠኝ ቀናት ሲሰጥ የቆየውን ሥልጠና ዛሬ አጠናቋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደ ሃና በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ ርብርብ እያደረገ ነው።
ይህንንም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ተግባራት አዲሱን የትምህርት ፍኖተ ካርታ ተከትሎ የሚከናወኑ መሆናቸውን ነው የገለጹት።
በዚህም ዩኒቨርሲቲው ለአመራሮችና የማኔጅመንት አባላትን አቅም ለማጎልበት የሥልጠና ማዕከላትና ሠነድ በማዘጋጀት ሥልጠና እየሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሥልጠናው የአመራሩን አቅም በመገንባት ዩኒቨርስቲው ተልዕኮውን በአግባቡ ለመፈጸም ያስችለዋል ብለዋል፤ በቀጣይም ለሌሎች የመንግሥትና የግል ተቋማት የሚሰጥ ይሆናል ነው ያሉት።
ዩኒቨርስቲው በሥልጠናው የሚያገኘው የአቅም ግንባታ፤ አገሪቱ የምትፈልገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል በበቂ ክህሎትና ጽንሰ ሃሳብ ለማውጣት ያስችለዋል ብለዋል።
ጎን ለጎንም የተለያዩ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ ዩኒቨርሲቲው ለማኅበረሰቡ ያለውን አበርክቶ ከፍ ለማድረግ እንደሚያስችል ጠቁመዋል።
ሥልጠናውን ሲከታተሉ የቆዩት አመራሮች በበኩላቸው፣ ሥልጠናው ዩኒቨርስቲው የራሱን የአስተዳደር ሥርዓት ለማሳለጥ ትልቅ እገዛ ያደርጋል ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው የሚሰጠውን የትምህርት እንዲሁም በርካታ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደሚያግዝም ተሳታፊዎቹ ጠቁመዋል።