ቀጥታ፡

የክብር ማሕተም የሆነውን የዓድዋ ድል ስናከብር የሀገር አንድነትን የሚጠብቁ ተግባራትን በማከናወን ሊሆን ይገባል_ብርጋዴር ጄኔራል ጌታቸው አሊ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 18 ቀን 2015 የኢትዮጵያ ብሔራዊ የክብር ማሕተም የሆነውን የዓድዋ ድል ስናከብር የሀገር አንድነትን የሚጠብቁ ተግባራትን በማከናወን ሊሆን ይገባል ሲሉ ብርጋዴር ጄኔራል ጌታቸው አሊ ገለጹ።

127ኛውን የአድዋ ድል በዓል በማስመልከት ተማሪዎች፣ የመገናኛ ብዙኃንና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በመከላከያ ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ ጦር አካዳሚ ጉብኝት አድርገዋል።

ኢትዮጵያ በሀገር መከላከያ ዘርፍ ያከናወነቻቸው የለውጥ ስራዎችና በአካዳሚው የሚገኙ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ምልከታ ተደርጓል።

በኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ በዓሉን የሚያንጸባርቁ ሁነቶችና የኪነ ጥበብ ሥራዎች በአካዳሚው እጩ መኮንኖች ቀርቧል።

በመርሐ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ የጦር አካዳሚ አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ጌታቸው አሊ 127ኛውን የአድዋ ድል ስናከብር ኢትዮጵያ በጽኑ ልጇቿ ያስከበረችውን ሉዓላዊነት በማሰብ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

የዓድዋ ጦርነት መነሻ የሆነው የውጫሌ ውል ሀገርን የመቀራመትና የቅኝ ገዥዎች ጥገኛ የማድረግ ዓላማ እንደነበርውም አስታውሰዋል።

በዓድዋ ጀግኖች አርበኞች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ሴቶችና አካል ጉዳተኞች ሳይቀሩ ከ1ሺ ኪሎ ሜትር በላይ በመጓዝ ለሀገራቸው ነጻነት በደማቸው ታሪክ ጽፈዋል ሲሉም ገልጸዋል።

ዓድዋ ለሀገራችን የድል ቀን በመላው ዓለም ለሚገኙ የጥቁር ህዝብ ደግሞ የነጻነት በዓል መሆኑን ገልጸው፤ ይህንን እውነት በሚገልጽና በሚያስገነዝብ መልኩ በዓሉን ልናከብረው ይገባል ሲሉ አመልክተዋል።

ዓድዋ "የኢትዮጵያ ብሔራዊ የክብር ማሕተም ነው" ሲሉ ያወሱት ብርጋዴር ጄኔራል ጌታቸው፤ በደምና በአጥንት የተገኘውን ዓድዋ ስንዘክር የሀገርን አንድነት የሚጠብቁ ተግባራትን ልናከናውን ያስፈልጋል ብለዋል።

ጀግኖች አባቶቻችን ያለ ዘር፣ ሃይማኖትና አካባቢ ልዩነት በደማቸው ያጸኗትን ሀገር እኛም እድገትና አንድነቷን የሚያስቀጥሉ ሥራዎችን በመተግበር ልናሳይ ይገባል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ጦር አካዳሚ በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በ1927 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን፤ የመከላከያ ሠራዊትንና ሀገርን የመሩ በርካታ መኮንኖችን ያፈራ አንጋፋ ወታደራዊ አካዳሚ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም