ቀጥታ፡

የፖላንድ የህክምና ባለሙያዎች በኢትዮጵያ ለአሥር ቀናት የሚቆይ ነጻ የህክምና አገልግሎት ሊሰጡ ነው

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 18/2015 የፖላንድ የህክምና ባለሙያዎች በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድና በጦርሃይሎች ኮምፕሬንሲቭ ሆስፒታሎች ለአስር ቀናት የሚቆይ ነጻ የህክምና አገልግሎት ሊሰጡ ነው።

ነጻ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት 30 የህክምና ባለሙያዎች የያዘው ቡድን ዛሬ ማለዳ ላይ አዲስ አበባ ሲደርስ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቀባበል ተደርጎለታል።

 የህክምና ቡድኑ በአገር ውስጥ አስቸጋሪ ለሚባሉ የሕክምና ጉዳዮች ይዘው በመጡት ዘመናዊ የህክምና መሳሪያ ጭምር በመታገዝ አገልግሎት እንደሚሰጡ ተጠቁሟል።

 የህክምና ቡድኑ አስተባባሪ ዶክተር ብዙአየሁ መንገሻ፤ ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው የህክምና ቡድን በቆይታው ለበርካታ ኢትዮጵያዊያን አገልግሎት ይሰጣል ብለዋል።  

የህክምና ቡድኑ የተለያየ ስብጥር ያለው መሆኑን ገልጸው የወገን ስብራትን የሚጠግኑ ስፔሻሊስቶች፣ የጭንቅላት ቀዶ ጥገና የሚከውኑና ሌሎችንም የህክምና እርዳታ ይሰጣሉ ነው ያሉት።

 ባለፈው ዓመት በነበራቸው ቆይታ በኢትዮጵያ ተሰጥተው የማያውቁ ህክምና አገልግሎቶችን መስጠታቸውን ጠቁመው በዚህም ዓመት የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል።

 ሁሉም ኢትዮጵያዊ ባለው የሙያ መስክ ህዝብንና አገሩን ማገልገል እንዳለበት የገለጹት ዶክተር ብዙአየሁ አገርን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

በተለይም በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ከትውልደ ፖላንዳዊ የህክምና ቡደኑ ከራስ አልፎ ለሌሎች መድረስን በመማር ለአገራቸው የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለባቸውም ጥሪ አቅርበዋል።

 የህክምና ቡደኑ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ አገልግሎት እንዲሰጥ ያስተባበረው የመከላከያ ድጋፍ ሰጪ አባል ቢኒያም መርዕድ፤ ቡድኑ ራሱ ይዞ በመጣው ዘመናዊ መሳሪያ በመታገዝ የህክምና አገልግሎት ያከናውናል ብሏል።

 በተለይም በመሳሪያ እጥረት በአገር ውስጥ ለማይሰጡ የህክምና ዓይነቶችን በመስጠት ለአገር ውስጥ የህክምና ባለሙያዎች ልምዳቸውን ያካፍላሉ ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል። 

በጦርሃይሎች ኮምፕሬንሲቭ ሆስፒታል የሥልጠናና ምርምር ዳይሬክተር ኮሎኔል አሰማ ተፈራ በበኩላቸው ቡድኑ ለበርካታ ኢትዮጵያዊያን አርዓያ የሚሆን ተግባር የሚያከናውን በመሆኑ ምስጋና ይገባዋል ብለዋል።

 በአቀባበል መርሃ ግበሩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበር ፕሬዝዳንት እድሪስ መሃመድ በሰጡት አስተያየትም ዳያስፖራው በአገር ውስጥ በልማት ሥራ ላይም ይሁን በተለያዩ አገልግሎት ላይ መሰማራት ቢፈልግ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ የሚያደርጉ መሆኑን ገልጸዋል።

 ሁሉም ዳያስፖራ ለአገሩ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።

 የህክምና ቡድኑ በየዓመቱ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ተመሳሳይ አገልግሎት ለመስጠት እቅድ እንዳለው ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም