“በኢትዮጵያ ታምርት'' ንቅናቄ ከግብርናው ወደ ኢንዱስትሪ ለመሸጋገር በኢኮኖሚው ዘርፍ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት እየተሰራ ነው - አቶ መላኩ አለበል - ኢዜአ አማርኛ
“በኢትዮጵያ ታምርት'' ንቅናቄ ከግብርናው ወደ ኢንዱስትሪ ለመሸጋገር በኢኮኖሚው ዘርፍ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት እየተሰራ ነው - አቶ መላኩ አለበል
ባህር ዳር (ኢዜአ) የካቲት 18/2015 መንግስት “በኢትዮጵያ ታምርት'' ንቅናቄ ከግብርናው ወደ ኢንዱስትሪ ለመሸጋገር በኢኮኖሚው ዘርፍ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት እየሰራ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ገለጹ።
በዘንድሮው ዓመት የአምራች ኢንዱስትሪው እድገት ወደ 10 ነጥብ 6 በመቶ ለማሳደግ መታቀዱን ጠቁመዋል።
የፌደራል እና የክልል የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ''የኢትዮጵያ ታምርት'' ንቅናቄ መድረክ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በኢትዮጵያ በአምራች ኢንዱስትሪው ላይ የተመሰረተ እድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በዚህም ''የኢትዮጰያ ታምርት'' ንቅናቄ በመምራት በሁሉም ክልሎች ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት የተሰራው ስራ በብዙ ችግሮች አልፎ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፈው አመት 4 ነጥብ 6 በመቶ የነበረውን የአምራች ኢንዱስትሪ እድገት ዘንድሮ ወደ 10 ነጥብ 6 በመቶ ለማሳደግ መታቀዱን ጠቁመዋል።
በአምራች ኢንዱስትሪው የሚፈጠረው የስራ እድል የተፈጠረላቸው ዜጎች ከ340 ሺህ በላይ ማለፉን ነው ሚኒስትሩ ያስረዱት።
የአማራ ክልል ለኢንቨስትመንት በሰጠው ትኩረት በአምራች ኢንዱስትሪው አበረታች ለውጥ አምጥቷል ብለዋል።
የአገር ውስጥ እና የውጭ ባለሃብቶች ማምረት የሕልውና መሰረት መሆኑን በመገንዘብ የጀመሩትን የኢንቨስትመንት ስራ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
መንግስት በኢንቨስትመንት ዘርፉ የነበሩ ማነቆዎችን ደረጃ በደረጃ የመፍታት እንቅስቃሴ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመልክተዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በበኩላቸው በአምራች ዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ክልሉ በየደረጃው የኢንቨስትመንት ቦርድ አቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን ገልጸዋል።
የቦርዱ ዋና ግብ ባለሃብቶች የሚያቀርቡትን የቦታ እና ሌሎች ጥያቄዎችን በአፋጣኝ መፍታት የሚያስችል መሆኑን አመልክተዋል።
ክልሉ የማዕድን፣ የቱሪዝም፣ ግብርና፣ አግሮ ፕሮሰሲንግና ሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎች እምቅ ፀጋ ያለው ነው ብለዋል።
የአገር ውስጥ እና የውጭ ባለሃብቶች በክልሉ የተመቻቸውን የኢንቨስትመንት ሁኔታ በመጠቀም መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ርዕሰ መስተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ከንቅናቄ መድረኩ ጎን ለጎን የኢንዱስትሪና የግብርና ምርቶችን የሚያሳይ የኤግዚቢሽንና ባዛር ተከፍቷል።