ቀጥታ፡

የአፍሪካ ልማት ባንክ የኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ ለማሳደግና የመሰረተ ልማት ስራዎችን ለማጠናከር ድጋፍ እያደረገ ነው- የባንኩ ፕሬዝዳንት አኪንውሚ አዴሲና

አዲስ አበባ(ኢዜአ) የካቲት 18/2015 የአፍሪካ ልማት ባንክ የኢትዮጵያ የግብርና ዘርፉን ለማሳደግና የመሰረተ ልማት ስራዎች ለማጠናከር ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የባንኩ ፕሬዝዳንት አኪንውሚ አዴሲና ተናገሩ።

አህጉራዊ ባንኩ የኢትዮጵያ የተለያዩ የልማት ሥራዎች ለማገዝ የ1 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ፕሬዝዳንቱ ለኢዜአ ገልጸዋል።

የግብርና ምርታማነትን ለሚያሳድጉ የአግሮ ኢንዱስትሪ ማቀነባበሪያና ለግብርና ምርት እሴት ልዩ ትኩረት በመስጠት ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ለጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናን በኃይል ለማስተሳሰር የምታደርገውን ጥረት ባንኩ እየደገፈ ይገኛል ብለዋል።

በአፍሪካ ከፍተኛ ስኬት እያስመዘገበ የመጣውን የግብርና ዘርፍ በመደገፍ አህጉሪቷ የምግብ ዋስትናዋን እንድታረጋግጥ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ዘርፉም እድገት እያሳየ መሆኑን ነው የባንኩ ፕሬዝዳንት የገለጹት።

ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በቆላማ አካባቢዎች እያካሄደች የምትገኘውን የስንዴ ምርታማነት ግቡን እንዲመታም ባንኩ ድጋፍ ማድረጉንም አመልክተዋል።

በተለይም በተሰራጨው የተሻሻለ የስንዴ ዝርያም ኢትዮጵያ የስንዴ ምርትና ምርታማነቷን በመጨመር የሚበረታታ ስራ መስራቷንም ነው ፕሬዝዳንቱ ያስረዱት።

የአፍሪካ ልማት ባንክ ድህነትን በመዋጋት የአፍሪካን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እድገት ማሳለጥ የሚችሉ የልማት መርሐግብሮችን በመቅረጽ እየሰራ የሚገኝ የፓን አፍሪካኒዝም የፖሊሲ ባንክ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም