አይ.ኤም.ኤፍ ለኢትዮጵያ በሰጠው ምክረ-ሀሳብ መሰረት የወጪ ንግድን ለማሳደግ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አይ.ኤም.ኤፍ ለኢትዮጵያ በሰጠው ምክረ-ሀሳብ መሰረት የወጪ ንግድን ለማሳደግ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ መስከረም 26/2011 ዓለምአቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ.ኤም.ኤፍ) ለኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ዕድገት በሰጠው ምክረ-ሀሳብ መሰረት ዘርፉን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር አስታወቀ። አይ.ኤም.ኤፍ የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ በፍጥነት ካልተሻሻለ ከፍተኛ አደጋ ላይ ነው ብሏል። በቅርቡ የተቋሙ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች የኢትዮጵያ ዓመታዊ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለመገምገም አዲስ አበባ መምጣታቸው ይታወሳል። በዚሁ ጊዜ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር የተወያዩ ሲሆን ኢትዮጵያ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2018/19 ዘመን 8 ነጥብ 3 በመቶ ዕድገት እንደምታስመዘግብ ትንበያቸውን አስቀምጠዋል። ተቋሙ የኢኮኖሚ ዕድገቱን ትንበያ በጥቅል ያስቀመጠ ሲሆን ዝርዝር ጉዳዮችን ወደፊት ያሳውቃል ተብሎ ይጠበቃል። የስምንት በመቶ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገት ትንበያ መነሻ ደግሞ የግሉ ዘርፍ የኢንቨስትመንት ዕድገት የመሰረተ-ልማት መስፋፋትና የወጪ ንግድ የማደግ ዕድል መኖር ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በቅርቡ ተግባራዊ እንዲሆን ያደረጉት በመንግሥት ስር የነበሩ ተቋማትን ለግል ባለሃብቶች በሽያጭ መልክ ማዘጋጀትም ለትንበያው አንዱ መነሻ ሆኗል። የመንግስት የብድር ቅነሳም አገሪቱ በዚህ ዓመት እንደምታሳካው ለተቀመጠው የ8 ነጥብ 3 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት የራሱ አስተዋፅኦ አለው ተብሏል። የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አድማሱ ነበበ ተቋሙ የተነበየው የአገሪቷ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገት ተስፋ ሰጪ መሆኑን ነው ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የተናገሩት። አይ ኤም ኤፍ የወጪ ንግዱ ቀይ መስመር ላይ ያለ ቢሆንም የአገሪቱ ሰላምና መንግስት የጀመረው የኢኮኖሚ ማሻሻያ የወጪ ንግዱን ለማሳደግ የሚያስችሉ መልካም ዕድሎች መሆናቸውን መተንበዩንም አስረድተዋል። ተቋሙ የአገሪቷ የወጪ ንግድ በፍጥነት እንዲሻሻል በሰጠው ምክረ-ሀሳብ መሰረት ዘርፉን የሚያሳድጉ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንም ነው የገለጹት። እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ ተቋሙ በወጪ ንግዱ፣ በመንግስትና በግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት እንዲሁም በገንዘብና የታክስ ስርዓት ማሻሻያ ላይ ምክረ-ሀሳቦችን አቅርቧል። በተለይም የወጪ ንግዱ ከፍተኛ አደጋ ላይ በመሆኑ በፍጥነት ሊሻሻል እንደሚገባና ለዚህ ደግሞ ተቋሙ ድጋፍ እንደሚያደርግ ማሳወቁን ይናገራሉ። ዓለምአቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ.ኤም.ኤፍ) የአገራትን የምጣኔ ሃብት ዕድገት በመተንበይ ይፋ የሚያደርግ ሲሆን ኢትዮጵያ የዚህ ተቋም አባል የሆነችው እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ1945 ነበር።