ቀጥታ፡

የኮሪያ ዘማቾች የፈጸሙት አኩሪ ታሪክ እኛም ከአገራችን አልፎ ለዓለም ሰላም መስዋዕት እንድንከፍል የሚያነሳሳ ነው - የአገር መከላከያ ሰራዊት አባላትና አመራሮች

አዲስ አበባ(ኢዜአ) የካቲት 18/2015 በኮሪያ ጦርነት የዘመቱ ኢትዮጵያውያን የፈጸሙት አኩሪ ታሪክ እኛም ከኢትዮጵያ አልፎ ለዓለም ሰላም መስዋዕት በመክፈል የአገራችንን ስም ከፍ እንድናደርግ የሚያነሳሳ ነው ሲሉ የመከላከያ ሰራዊት አባላትና አመራሮች ተናገሩ።

ኢትዮጵያ በኮሪያ ጦርነት እንድትሳተፍ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በቀረበላት ጥያቄ መሰረት እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ከግንቦት 1950 እስከ ሐምሌ 1953 በተካሄደው ጦርነት ላይ 6 ሺህ 37 ሠራዊት አሰማርታ በጀግንነት ለኮሪያ ሰላምና ነጻነት ተዋግታለች።

ወታደሮቹ በ32ኛ ሬጅመንት 7ኛው የአሜሪካ ዲቪዚዮን ሥር ሆነው በሻንያንግኒ አጠገብ በቾኩንሳን ካነግዎን ግዛት ሸለቆዎች በተካሄዱ 253 ጦርነቶች ተሳትፈዋል።

በአምስት ሻለቃዎች ወደ ውጊያ የገባው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ከኮሪያ ሪፐብሊክና ከአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች የክብርና የጀግንነት ሜዳይ ተሸልሟል።

የቃኘው ሻለቃ ጦር እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር መስከረም 16 እስከ 21 ቀን 1951 በሙንዳግ-ኒ ለተደረገው ጦርነት በአሜሪካን ፕሬዚዳንት እንዲሁም እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ግንቦት 20 1953 በቾልዎን ሰሜን ምዕራብ ለተደረገው ጦርነት በኮሪያ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ተሸልሟል።

ወደ ኮሪያ የዘመተው የኢትዮጵያ ጦር ከያዘው መሬት አንድ 'ኢንች' እንኳ ያልሰጠና አንድም ወታደር በምርኮ ያልተወሰደበት ጦር ነው።

ኢትዮጵያውያን የአገራቸውን ልዩና ከፍተኛ የውጊያ ችሎታ ያሳዩበትና ኢትዮጵያውያን በተፈጥሮ ተዋጊ ናቸው የሚለውን ሐሳብ ያረጋገጡበት ነው።

እነዚህ ጀግኖች በአዲስ አበባ የኢትዮጵያ ኮሪያ ዘማቾች መታሰቢያ ፓርክ፣ ሀውልትና ሙዚየም በስማቸው ተሰይሞላቸዋል።

የአገር መከላከያ ሰራዊት አባላትም የመታሰቢያ ፓርኩን የጎበኙ ሲሆን በጉብኝታቸው ቀደምት ኢትዮጵያውያን የአገራችን ዳር ድንበር ከማስከበር ባለፈ ከኮሪያ ጀምሮ ለዓለም ሰላም ያሳዩትን ጀግንነት መመልከታቸውን ተናግረዋል።

በተለይም ከአድዋ ጀግኖች አባቶቻቸው የወረሱትን የድል ታሪክን የመድገም ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን እንደተወጡም መስክረዋል።

በተለይም ከዘመቱት ኢትዮጵያውያን ውስጥ አንድም ወታደር አለመማረኩና ሰንደቅ ዓላማዋን በክብር ይዘው እንደተሸኙ በክብር ከፍ አድርገው መመለሳቸው የሚደንቅ ነው ብለዋል።

በዚህም ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው ጉልህ ታሪክ በመጻፍ ለተቀረውም ዓለም ሰላምና ደህንነት የሚተርፍ ስራ እንደሚሰሩ ተምረናል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ የኮሪያውን የሰላም ማስከበር ተልዕኮዋን በማጠናከር አፍሪካውያን ከቅኝ ገዛት ነጻ እንዲወጡ ያደረገችውን ጉልህ ተጋድሎ አሁንም በሰላም ማስከበር በመድገም ላይ መሆኗን ተናግረዋል።

ለዚህም በሶማሊያና በደቡብ ሱዳን ጭምር ኢትዮጵያውያን ወታደሮች ሰላም የማስፈን ተልዕኳቸውን በብቃት እየተወጡ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኮሪያ ዘማቾችን የጀግንነት ታሪክ መውረሳቸውን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ በቀጣይ በዓለም ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ጉልህ ሚና እንትድጫወት በማድረግ የራሳቸውን ታሪክ ለመጻፍ ዝግጁ መሆናቸውን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም