ቀጥታ፡

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 15ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ኢትዮጵያ ቡና ከፋሲል ከነማ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል

አዲስ አበባ(ኢዜአ) የካቲት 18/2015፦ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 15ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ኢትዮጵያ ቡና ከፋሲል ከነማ ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከምሽቱ 1 ሰአት በድሬዳዋ ስታዲየም ይከናወናል።

ኢትዮጵያ ቡና በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው 14 ጨዋታዎች አምስት ጊዜ ሲያሸንፍ በተመሳሳይ አምስት ጊዜ ተሸንፏል። አራት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።

ቡናማዎቹ 20 ግቦችን አስቆጥረው 18 ግቦች አስተናግደዋል። በሁለት የግብ ክፍያ በ19 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

ኢትዮጵያ ቡና በውድድር ዓመቱ መጀመሪያ ከውጤት ማጣት ጋር በተያያዘ አሰልጣኝ ተመስገን ዳናን ማሰናበቱ የሚታወስ ነው። ዮሴፍ ተስፋዬ ክለቡን በጊዜያዊነት በመምራት ላይ ይገኛል።


ተጋጣሚው ፋሲል ከነማ በዘንድሮው የውድድር ዓመት ወጥነት ያለው አቋም እያሳየ አይገኝም።

ክለቡ እስከ አሁን ባደረጋቸው 14 ጨዋታዎች አምስት ጊዜ ሲያሸንፍ አራት ጊዜ ደግሞ ተሸንፏል። አምስት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።


14 ግቦችን ሲያስቆጥር 11 ግቦችን አስተናግዷል። በሶስት የግብ እዳ በ20 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።


ፋሲል ከነማ በበኃይሉ ነጋሽ(ቲጋና) ምትክ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ክለቡን እስከ ውድድር ዓመቱ መጨረሻ ድረስ እንዲመሩ መሾሙ ይታወቃል።

የሁለቱ ክለቦች ደጋፊዎች ለጨዋታው ከፍተኛ የሆነ ድምቀት ይሰጡታል ተብሎ ይጠበቃል።

ኢንተርናሽናል ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ ተጠባቂውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

በሌላኛው የ15ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ከቀኑ 10 ሰአት በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኙት ሲዳማ ቡና እና ኢትዮ ኤሌትሪክ ይጫወታሉ።

ሲዳማ ቡና በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ 14ኛ እንዲሁም ኢትዮ-ኤሌትሪክ 15ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።


በተያያዘ ዜና ትናንት በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 15ኛ ሳምንት ጨዋታ ኢትዮጵያ መድህን በያሬድ ዳርዛ ብቸኛ ግብ ሀዲያ ሆሳዕናን 1 ለ 0 በማሸነፍ ወሳኝ ሶስት ነጥብ አግኝቷል።


ውጤቱንም ተከትሎ ኢትዮጵያ መድን ነጥቡን ወደ 30 ከፍ በማድረግ የሊጉን መሪነት በጊዜያዊነት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ተረክቧል።


ትናንት በ15ኛ ሳምንት በመቻል እና በለገጣፎ ለገዳዲ መካከል መደረግ ነበረበት።

ይሁን እንጂ የለገጣፎ ለገዳዲ ተጫዋቾች በውድድር ደንብ ከተቀመጠው ቁጥር በታች(አራት) ሆነው መገኘታቸውን የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር አስታውቋል።


የተጫዋቾቹ ቁጥር ያነሰበት ምክንያት ክለቡ በሁለተኛው ዙር የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ያስፈረማቸውን ተጫዋቾች የመጀመሪያው ዙር የሊጉ ውድድር ሳይጠናቀቅ መጠቀም ስለማይችል መሆኑ ተገልጿል።


የመቻል ተጫዋቾች ሜዳ ገብተው 30 ደቂቃ ከቆዩ በኋላ መቻል በፎርፌ ውጤት እንዲያሸንፍ ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም