ኢትዮጵያ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ስርዓትን በማስፈን የውሃ ሀብትን በፍትሐዊነት ለማድረስ እየሰራች ነው-ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ስርዓትን በማስፈን የውሃ ሀብትን በፍትሐዊነት ለማድረስ እየሰራች ነው-ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 17/2015 ኢትዮጵያ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ስርዓትን በማስፈን የውሃ ሀብት በፍትሐዊነት ለማድረስ እየሰራች መሆኑን የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ ገለጹ።
የዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት(ፋኦ) በብሔራዊ የውሃ ፍኖተ ካርታዎች ዙሪያ ለሶስት ቀናት በዚምባቡዌ ሲያካሂድ የነበረው አውደ ጥናት ዛሬ ተጠናቋል።
የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስተር ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ የኢትዮጵያ የውሃ ሀብት አጠቃቀም ልምድን ለአውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች አካፍለዋል።
ኢትዮጵያ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ስርዓትን በማስፈን የውሃ ሀብት በፍትሐዊነት ተደራሽ ለማድረግ እየሰራች መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ለውሃ ሀብት መበልጸግ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።
የውሃ እጥረትን መቋቋም የሚችል የክላስተር ስንዴ ግብርና ውጤታማነት በተሞክሮ ሊወሰድ እንደሚገባው አመልክተዋል።
ከመንግስት የሚመደበውን በጀት ከልማት አጋሮች የሚደረገውን ድጋፍ በማቀናጀት ዜጎችን የንጹህ ውሃ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ሚኒስትሩ አስረድተዋል።
ከኢነርጂ ልማት አኳያም የአረንጓዴ ኃይል ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸው ለጎረቤት አገራትም ጭምር የኤሌክትሪክ ኃይል እየላከች እንደምትገኝ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ያላትን ውስን የውሃ ሀብት ለመጠቀም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ሚኒስትሩ አክለዋል።
በአውደ ጥናቱ ላይ የአፍሪካ አገራት የውሃ፣ የግብርና እና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሚኒስትሮች እና የዘርፉ አመራሮች መሳተፋቸው ተገልጿል።
የዚምባቡዌው ውይይት እ.አ.አ መጋቢት 2023 ማርች ወር ላይ በኒው ዮርክ ከተማ ለሚደረገዉ ለተባበሩት መንግስታት የውሃ ጉባኤ ‘UN Water Conference’ ዝግጅት እንዲያግዝ ታስቦ መሰናዳቱ ተገልጿል።