ቀጥታ፡

መጪው ምርጫ ተአማኒና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን መንግስት ኃላፊነቱን ይወጣል - ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ

አዲስ አበባ መስከረም 26/2011 መጪው ምርጫ ተአማኒና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን መንግስት ከፍተኛውን ኃላፊነት እንደሚወጣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለፁ። በሐዋሳ ስቴዲዮም በተካሄደው የኢህአዴግ 11ኛው ጠቅላላ ጉባኤ የመዝጊያ ስነ-ስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በአገሪቱ የተጀመረው የዴሞክራሲ ምህዳር የማስፋት ሂደት የይስሙላ አይደለም ብለዋል። በመሆኑም የምርጫ ቦርድና የሰብአዊ መብት ኮሚሽንን ጨምሮ ሁሉም የዴሞክራሲ ተቋማት አሰራራቸውን የማዘመንና በአመራር የማጠናከር ሥራ እንዲሰሩ የኢህአዴግ ጉባኤ አቅጣጫ ማስቀመጡን አረጋግጠዋል። ከዚህ በተጨማሪ መጪው ምርጫ በህዝብ፣ በሚፎካከሩ ፓርቲዎች እና ምርጫውን ለመታዘብ በሚመጡ አገሮችና አህጉራዊና አለም አቀፍ ድርጅቶች የታመነ እንዲሆን መንግስት ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚጫወት ጉባኤተኛው አቅጣጫ አስቀምጠዋል ነው ያሉት። "ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ይሁን ሲባል አሁን እያስተዳደረ ያለው ፓርቲ የህዝብ ይሁንታ እስካገኘ ድረስ ይሁንታም በብዙሃንም እስከታመነ ድረስ ይቀጥላል" ነው ያሉት። ተፎካካሪ ፓርቲዎች አሁን ካሉበት የተበተነ ሁኔታ ሰብሰብ በማለት አማራጭ ለመሆን የሚያስችል ቁመና ይዘው እንዲመጡም አሳስበዋል። “ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን በምርጫ ውድድሩ መሸነፍም እንዳለ በእኛም በእናንተም በኩል አስበን” በምርጫው ማሸነፍ ሳይሆን ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ኢትዮጵያ ውስጥ ማምጣት እንደሚገባ ሁላችንም አምነን በጋራ መስራት አለብን" ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል። አራቱ የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ባካሄዱት ጉባኤ አዳዲስ ምሁራን ወጣቶችና ሴቶች ወደ ድርጅት አመራር ወደፊት የመጡበት ምክንያት የተሻለ መንግስት ለመሆንና የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል ቁመና ለመፍጠር ነው ብለዋል። ኢህአዴግ በምርጫም ይሁን በልማት ጉዳዮች ተገዳድሮ አያውቅም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢህአዴግን መፎካከር የሚፈልጉ ኃይሎች በአዲስ ኃይል በአዲስ አስተሳሰብ በወጣቶች ባላረጀ የአመራር መንገድ እንዲመጡ፤ ይህ ካልሆነ ግን ፉክክሩ ከባድ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል። “እኛ በአዲስ ጉልበት በአዲስ ብልሃት ስንመጣ በዚያ መንገድ ያልመጣችሁ ፓርቲዎች ከወዲሁ ሽንፈት የሚሰማችሁ ከሆነ በኛ በኩል ልምድ ለማካፈል፣ ምክር ለመስጠት፣ በስልጠና ለማገዝና እናንተን ለማጠናከር አዲስ ኃይል ከናንተም ወገን እንዲወጣ ፍላጎት ያለን መሆኑን ልንገልፅላችሁ እንፈልጋለን” የሚል መልዕክት ለተፎካካሪ ፓርቲዎች አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም