ቀጥታ፡

የጥጥ መዳመጫ ማሽን መለዋወጫ አቅርቦት ፈተና ሆኖብናል-የጥጥ መዳመጫ ፋብሪካዎች

ሞጆ መስከረም 26/2011 የጥጥ መዳመጫ ማሽን መለዋወጫ አቅርቦት እንደተቸገሩ የጥጥ መዳመጫ ፋብሪካዎች ተናገሩ። ፋብሪካዎቹ ይህንን ያሉት የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የስራ ኃላፊዎች በዱከምና ሞጆ የሚገኙ የጥጥ ፋብሪካዎችን ወቅታዊ የስራ እንቅስቃሴ በጎበኙበት ወቅት ነው። በዚህ ወቅት በዱከም ከተማ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በገበሬዎች የተመረተ ጥጥ በመዳመጥ ለጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች የሚያቀርበው 'ዶሪ ከበደ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር' የማሽን መለዋወጫ እጥረት በስራው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ መፍጠሩን ነው የተናገረው። የማህበሩ ስራ አስኪያጅ ሻምበል ሞገስ ሰለሞን የጥጥ መዳመጫ ፋብሪካው የማምረት አቅሙ ያሽቆለቆለው በማሽኑ መለዋወጫ እጥረት ምክንያት እንደሆነ ተናገሯል። "ድርጅቱ በዓመት እስከ 100 ሺህ ኩንታል ጥጥ ያመርት ነበር "ያሉት ስራ አስኪያጁ፤ በአሁኑ ወቅት ግን በመለዋወጫ እቃዎች እጥረት ምክንያት ከ65 ሺህ እስከ 70 ሺህ ኩንታል ለማምረት መገደዱን ነው የተናገሩት። ችግሩን ያባባሰው የጥጥ መዳመጫ መለዋወጫዎቹ አገር ውስጥ የማይገኙ መሆኑ ነው ያሉት ስራ አስኪያጁ የውጭ ምንዛሬን ለማግኘት ከፍተኛ ችግር ሆኖብናል ብለዋል። በተመሳሳይ 'የገብረሰላም  የጥጥ መዳመጫ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር' ስራ አስኪያጅ አቶ ብርሃነ ወልደምህረት በ2010ዓ.ም የማሽን መለዋወጫ መሳሪያ ባለመኖሩ ፋብሪካው ከሁለት ወር በላይ ስራ ለማቆም ተገዶ እንደነበር ተናግረዋል። በዚህም ምክንያት ፋብሪካው ቀደም ሲል በዓመት እስከ 70 ሺህ ቶን ጥጥ ያመርት ነበር ያሉት ሰራ አስኪያጁ በ2010 ዓ.ም ግን ከ50 ሺህ ቶን በታች ለማምረት መገደዱን አስታውሰዋል። የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ከፍተኛ የተዳመጠ ጥጥ አቅርቦት ጥያቄ አለ ያሉት ስራ አስኪያጁ ሆኖም ግን የመለዋወጫ እቃዎች አለመኖር ፍላጎቱን ለመሸፈን አዳጋች አድርጎብናል ብለዋል። በሞጆ ከተማ የእስቱዲዮ ስሪ ዲ መለዋወጫ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ አቶ አሰግድ ከበደ በበኩላቸው ከማሽን መለዋወጫ ባሻገር የመብራት መቆራረጥና የመስሪያ ቦታ እጥረት ፈተና እንደሆነባቸው ተናገረዋል። እንዲሁም አንዳንድ የጥጥ አምራች ገበሬዎች የሚያቀርቡት ጥሬ ጥጥ ከደረጃ በታች መሆን ሌላው ተግዳሮት መሆኑን አስታውሰዋል። የማሽን መለዋወጫው በአገር ውስጥ ያለመኖር ችግር መንግስት ፋብሪካዎቹ የውጭ ምንዛሬ አግኝተው ከውጭ የሚያስገቡበትን እድል እንዲያመቻችም አቶ አሰግድ ጠይቀዋል። የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የጥጥ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መሰለ መኩሪያ በበኩላቸው የጥጥ መዳመጫ ማሽኖች መለዋወጫ ማቅረብ ያልተቻለው እንደ ሀገር በተከሰተ የውጭ ምንዛሬ እጥረት መሆኑን ተናገረዋል። ኢንስቲትዩቱ በአሁኑ ወቅት ችግሩን ለመፍታት ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ አመራሮች ጋር በመነጋገር ኢንዱሰትሪዎቹ የውጭ ምንዛሬ የሚያገኙበትን ሁኔታ ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል። በ2010 ዓ.ም የምርት ዘመን 42 ሺህ ሜትሪክ ቶን ጥጥ እንደ ሀገር ተመርቶ 5 ሺህ ቶን ወደ ውጭ ተልኮ 7 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን አቶ መሰለ ተናግረዋል። ኢንስቲትዩቱ የሀገር ውስጥ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎችን ፍላጎት ለማሟላት ትኩረት ይሰጣል ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ከ100 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በምርት ለመሸፈን ቢታቀድም ከ60 ሺህ ሄክታር መሸፈኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም