ከአድዋ ጀግኖች በወረስነው ጀግንነት የሀገራችንን ሉዓላዊነት ለማስከበር በተጠንቀቅ ላይ እንገኛለን-የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት - ኢዜአ አማርኛ
ከአድዋ ጀግኖች በወረስነው ጀግንነት የሀገራችንን ሉዓላዊነት ለማስከበር በተጠንቀቅ ላይ እንገኛለን-የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት
የካቲት 15/2015 (ኢዜአ) የአድዋ ጀግኖች በደማቸው ያስረከቡንን ሀገር ሉዓላዊነት ለማስቀጠል መስዋዕት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ገለጹ።
ኢትዮጵያውያን ዳር ድንበሯን ሊደፍር የመጣውን የጣሊያን ወራሪ ኃይል ከአራቱም ማዕዘን በመሰባሰብ ደምና አጥንታቸውን በአድዋ ተራሮች በመከስከስ ዓለምን ያስደነቀ የጥቁር ህዝብ የድል ታሪክ ጽፈዋል።
በ1888ዓ.ም በአድዋ ላይ የተመዘገበው ድል የሰው ልጅ እኩልነትን አብስሯል።
ድሉ ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ያላቸውን ፍቅር እና የአንድነታቸውን የጥንካሬ ሚስጥር የገለጹበት ሲሆን ለአፍሪካውያን ደግሞ የፀረ ቅኝ ግዛትን ትግል እንዲያቀጣጥሉ የነጻነት ችቦን የለኮሰ ነው።
የድሉ 127ኛ ዓመት የመታሰቢያ ክብረ በዓል ከወዲሁ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል።
ዛሬ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላትና የመከላከያ ሚኒስቴር ሰራተኞች የኢትዮጵያ ኮሪያ ዘማቾች ብሔራዊ ፓርክን እንዲሁም የአድዋ ዜሮ ሙዚየም ፕሮጀክት ግንባታን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሰራዊቱ አባላት እንዳሉት፤ አድዋ የቀደምት ኢትዮጵያውያን የአንድነታቸው ተምሳሌት ነው።
የጎሳ፣ የሃይማኖት፣ የቋንቋ ልዩነት ሳይገድባቸው የሀገራቸውን ክብርና ሉዓላዊነት ለማስከበር በባዶ እግር ተጉዞው የጠላትን አከርካሪ በመስበር ድል ያስመዘገቡበት ታሪክ መሆኑን ገልጸዋል።
ድሉ ለአፍሪካውያንና በመላው ዓለም ላሉ ጥቁሮች የአሸናፊነት ተምሳሌት መሆኑንም ገልጸዋል።
አድዋ በየትኛውም የዓለም ክፍል ያለ ማህበረሰብ ሁሉ በሰውነቱ እኩል መሆኑን ያሳዬና ትልቅ የአስተሳሰብ ለውጥን ስለመፍጠሩም ተናግረዋል።
ለዚህ ዘመን ትውልድም ለሀገር ቀድሞ መገኘትን ያስተማረና በትውልዱ ላይ ትልቅ የአሸናፊነት ስነ-ልቦናን ያስታጠቀ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ጎብኝዎቹ አክለውም የዚህ ዘመን ትውልድ ግዙፉን የአባቶቹን የድል ታሪክ ለመዘከርና ከታሪኩም ለመማር የአድዋ ዜሮ ሙዚየም ፕሮጀክትን መገንባቱ የሚደነቅ ነው ብለዋል።
የሙዚየሙ ግንባታ የአድዋን ድል፣ የጀግኖችን ታሪክና አፍሪካውያንን በሚመጥን መልኩ እየተገነባ መሆኑ ለአደዋ ድል የተሰጠውን ከፍተኛ ዋጋ ያሳያል ሲሉ ገልጸዋል።
ሙዚየሙ ፓን አፍሪካኒዝምን ለማጠናከር እንዲሁም ለመጪው ትውልድ በታሪክ ላይ የተመሰረተ ድልን በየዘርፉ ለመድገም የሚያነሳሳ ነው ብለዋል።
የአድዋ ድል በዚህ ዘመን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ላይ "የጀግንነት ህዋስ ሆኗል" ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ፤ ሰራዊቱ ከአባቶቹ በወረሰው ጀግንነትና ጽናት ሀገሩን ሳያስደፍር መቀጠሉን ገልጸዋል።
ከቀደምት ኢትዮጵያውያን ጀግኖች የተማርነውን በአንድነት የመቆም የድል ሚስጥር በመድገምና ከሀገር በፊት ራስን በማስቀደም መስዋዕት ለመክፈል ዝግጁ ነን ብለዋል።