ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ለተፈናቃዮች 15 ሚሊየን ብር ግምት ያለው የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

ደብረ ብርሃን የካቲት 17/2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በደብረ ብርሃን ጊዜያዊ መጠለያ ለሚገኙ ወገኖች ከ15 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው የምግብና ሌሎች ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ ።

 በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የሰሜን ሸዋ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ዳምጠው እምሻው ድጋፉን ሲያስረክቡ እንደገለጹት በደብረ ብርሃን ከተማና አካባቢው በርካታ ተፈናቃዮች በችግር ውስጥ ይገኛሉ።

 ማህበሩም በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ያለውን ችግር በመገንዘብ ከዚህ በፊትም በተመሳሳይ የምግብ፣ አልባሳትና ሌሎች ቁሳቁሶችን ድጋፍ ማድረጉን አውስተዋል። 

ዛሬ ድጋፍ ከተደረጉት ቁሶች ውስጥም ብርድ ልብሶች፣ ምንጣፎች፣ ሳሙና የሴቶች ንጽህና መጠበቂያዎችና በጸሃይ ሃይል የሚሰሩ መብራቶች እንደሚገኙበት ገልጸዋል።

 ማህበሩ በቀጣይም የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ዳምጠው አስረድተዋል።

 በደብረ ብርሃን ከተማ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ የምትገኘው ወጣት ራህመት ሁሴን እንደገለጸችው በተፈጠረው ችግር ምክንያት ተፈናቅለው በመምጣት ደብረ ብርሃን መጠለላቸውን ተናግራለች።

አሁን ላይ መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ባለሀብቶችና ህብረተሰቡ የቻሉትን ድጋፍ እያደረጉላቸው ቢሆንም ካለው ተፈናቃይ ቁጥር ጋር ተያይዞ ድጋፉ ቀጣይ ሊሆን ይገባል ብላለች። 

በቅርቡ ደብረ ብርሃን መጠለያ ጣቢያ የደረሱት መምህር ሳዳም ሁሴን በበኩላቸው ከመንግስት ስራውና ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሎ መምጣቱን ተናግሮ ድጋፉ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ የቀይ መስቀል ማህበር ላደረገላቸው ድጋፍ አመሰግነው መንግስት በአካባቢዉ ዘላቂ ሰላም አስፍኖ ወደ ቀያቸዉ እንደመልሳቸዉ ጠይቀዋል ። 

በደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ብቻ ከተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ከ26ሺህ በላይ ዜጎች እንዳሉ ከከተማ አስተዳደሩ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም