ቀጥታ፡

ባለፉት ስድስት ወራት 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ለኢንተርራይዞች መሰራጨቱን የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዞች ልማት ኢንስቲትዩት ገለፀ

አዳማ፣ የካቲት 17 ቀን 2015 (ኢዜአ) ባለፉት ስድስት ወራት ለስራ ማስኬጃና ለተለያዩ የማምረቻ ማሽነሪዎች መግዣ የሚውል የ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ፋይናንስ ለኢንተርራይዞች መሰራጨቱን የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዞች ልማት ኢንስቲትዩት ገለፀ።

ኢንስቲትዩቱ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በግማሽ ዓመቱ አፈፃፀምና ቀጣይ አቅጣጫ ላይ እየመከረ ይገኛል። 

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዞች ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱልፈታህ ዩሱፍ በተለይ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ ባለፉት ስድስት ወራት ከ2 ሺህ 100 በላይ ኢንተርፕራይዞች ተደራጅተው ወደ ስራ ገብተዋል። 

የፋይናንስ በተለይ የስራ ማስኬጃና የተለያዩ የማምረቻ ማሽነሪዎች መግዣ የሚውል የብድር አገልግሎት መሰራጨቱን ገልጸው፤ በዚህም ወደ ስራ ለገቡ 2 ሺህ 196 ኢንተርፕራይዞች 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር የስራ ማስኬጃና 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የሊዝ ማሽን ጨምሮ ለማምረቻ ግብዓት የሚውል ብድር መሰጠቱን ጠቅሰዋል። 

በበጀት ዓመቱ 4 ሺህ 60 ኢንተርፕራይዞች ወደ ስራ ለማስገባት ታቅዶ በግማሽ ዓመት አፈፃፀም የተሳካ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል። 

ወደ ስራ የገቡ ኢንተርፕራይዞችን ጨምሮ ነባሮቹን በማጠናከር የተሻለ ምርትና ምርታማነት ውስጥ እንዲገቡ በመደረጉ 77 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል በዘርፉ መፈጠሩን አቶ አብዱልፈታህ ተናግረዋል። 

በግማሽ ዓመቱ ለኢንተርፕራይዞች ግንዛቤ ከመፍጠርና አቅም ከመገንባት አንፃር የተሻለ ስራ የተሰራ ቢሆንም ክፍተቶች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ በተለይ ለኢንተርፕራይዞች በባንኮች የሚጠየቀው የዋስትና ማስያዣ የፋይናንስ አቅርቦትን በሚፈለገው መልኩ እንዳይሆን አድርጎታል ብለዋል።

 በተመሳሳይ የመሬት፣ የመስሪያና መሸጫ ሼዶች፣ የሃይል አቅርቦት፣ የውሃና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ችግሮች አሁንም ዘርፉ በሚፈለገው ልክ እንዳይራመድ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

 ችግሮችን ለመቅረፍ በተለይ የህዝብ ክንፍ ከሆኑት ባንኮች፣ የንግድና ዘርፍ ተቋም፣ በየደረጃው ካሉ የዕለት ተዕለት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር በቅርበት እየሰራን ነው ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም