የኢንዱስትሪና ዩኒቨርሲቲ ትስስር በማጠናከር በዘርፉ የተያዙ ትልልቅ ግቦች እንዲሳኩ በልዩ ትኩረት ይሰራል-አቶ መላኩ አለበል - ኢዜአ አማርኛ
የኢንዱስትሪና ዩኒቨርሲቲ ትስስር በማጠናከር በዘርፉ የተያዙ ትልልቅ ግቦች እንዲሳኩ በልዩ ትኩረት ይሰራል-አቶ መላኩ አለበል
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 17/2015 የኢንዱስትሪና ዩኒቨርስቲዎችን ትስስር በማጠናከር በዘርፉ የተያዙ ትልልቅ ግቦች እንዲሳኩ ልዩ ትኩረት በመስጠት እየተሰራ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ገለጹ።
ሚኒስቴሩ ከዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር "በኢትዮጵያ ታምርት" አገራዊ ንቅናቄ ዙሪያ ውይይት ተካሂዳል።
በውውይቱ ላይ 150 የሚጠጉ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች የተገኙ ሲሆን በአምራች ኢንዱስትሪው መስክ እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት ዙሪያ ማብራሪያ ተሰጥቷል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት አምራች ኢንዱስትሪው ለወጪ ንግድ ከሚያቀርባቸው ምርቶች 9 ቢሊዮን ዶላር ለማገኘት እቅድ ተይዟል፡፡
ከስራ ዕድል ፈጠራ አኳያም 5 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር መታቀዱንም በመጥቀስ "አሁን ካለው የአምራች ኢንዱስትሪዎች ከ50 የማምረት አቅም ወደ 85 በመቶ ከፍ ለማድረግ ጥረቶች እየተደረጉ ነው" ብለዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት አገር አቀፍ ንቅናቄ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ወዲህ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች በአገር ውስጥ መተካት ላይ አበረታች ውጤቶች እየተገኙ መሆኑንም አብራርተዋል።
በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተያዙ አገራዊ ግቦች እንዲሳኩ የኢንዱስትሪ እና ዩኒቨርስቲዎች ትስስር ሊጠናከር እንደሚገባ ገልጸው ኢንዱስትሪው ማደግ የሚችለው የተማረ የሰው ሃይል ሲያገኝ ነው ሲሉም አመልክተዋል።
ኢንዱስትሪዎች በክህሎት ረገድ የሚታይባቸውን ከፍተት ለመሙላት ሚኒስቴሩ ኢንዱስትሪዎችና ዩኒቨርሲቲዎች ትስስር የሚያጠናክሩበትን እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቁመዋል።
የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ወሰንሰገድ አሰፋ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው አምራች ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን የሰው ሃይል ማፍራት ላይ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ወደ ዘርፉ የሚሰማሩ ሰልጣኞች በቅድሚያ በአገሪቷ እቅዶችና ግቦች ላይ መሰረታዊ ግንዛቤ ሊኖራቸው እንደሚገባ አስታውሰው መድረኩም ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።