ትውልዱ ጀግንነትና ጥበብን ከአድዋ በመማር የራሱን ታሪክ መስራት አለበት - ኢዜአ አማርኛ
ትውልዱ ጀግንነትና ጥበብን ከአድዋ በመማር የራሱን ታሪክ መስራት አለበት
የካቲት 17/2015 (ኢዜአ) የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ህዝቦች በጋራ ተጋድሎ ታሪክ የሰሩበት ድል በመሆኑ ትውልዱ ጀግንነትና ጥበብን ከድሉ በመማር የራሱን ታሪክ መስራት አለበት ሲሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ ገለጹ።
አድዋ፡ አንድነት፣ ጀግንነት እና ነፃነት" በሚል መሪ ሃሣብ 29ኛው የ"ጉሚ በለል" ውይይት በኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ተካሂዷል።
ውይይቱ ድሉ ከኢትዮጵያ አልፎ የመላው ጥቁር ህዝቦች የነጻነት ገድል ነፀብራቅ በመሆኑ የአሁኑ ትውልድ ከአድዋ ተምሮ ሀገሪቱን በልማትና በዴሞክራሲ ግንባታ ለማሻገር እንዲችል በሚያግዙ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው።
ከአድዋ ድል ምን እንማር? ምንስ ይዘን የድርሻችንን እናበርክት? የሚሉት ጉዳዮችም በውይይቱ የተካተቱ ናቸው።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጀላ በወቅቱ እንዳሉት፤ አድዋ የጥቁር ህዝቦች ምልክት፣ ኢትዮጵያን ያስተዋወቃትና ሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝቦች አንድ ያደረገ ድል ነው።
ልክ እንደ አባቶቹ ትውልዱ ጥበብና ጀግንነት ከአድዋ ድል በመማር በተሰለፈበት መስክ ሁሉ የሀገርን ሰላምና አንድነት አስጠብቆ የሚያስቀጥል ታሪክ መስራት አለበት ነው ያሉት።
አድዋ ህዝባዊነትና ኢትዮጵያዊነትን እንዳጎላ ሁሉ አሁንም በአንድነትና በሁለንተናዊ ጀግንነት የሀገሪቱን ከፍታ ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታዎች ውይይቱ ያተኮረባቸው ሌሎቹ ጉዳዮች ናቸው።
የውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የባህልና ፖለቲካ ተመራማሪው ዶክተር ሙሉጌታ ደበበ በበኩላቸው "እንደ ሀገር በርካታና በዓለም አዳባባይ ሊወሱ የሚገቡ ድሎች ቢኖሩንም አሁንም ረጅም ርቀት ይቀረናል" ብለዋል።
በትጋት፣ በአንድነትና በመደማመጥ ሀገርን ማሻገር ይገባናል ነው ያሉት ዶክተር ሙሉጌታ ።
የዓለም ጥቁር ህዝቦች ድል ከሆነው አድዋ በተጨማሪ አሁን ደግሞ በልማቱና በሰላሙ ለዓለም ህዝቦች አርአያ መሆን ይገባናል ያሉት ደግሞ ከውይይት ተሳታፊዎች መካከል አቶ ኢብሳ ነገዎ ናቸው።
የኢትዮጵያ አትሌቶች ማህበር ፕሬዝዳንት አትሌት ኮማንደር ማርቆስ ገነቴ በበኩሉ፤ አባቶች አጥንታቸውን ከስክሰው ያቆዩዋትን ሀገር እኛም በአንድነት ሆነን በልማቱ መስክ ሀገራችንን ማሻገር ይገባናል ብሏል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጀላ መርዳሣን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችና ታዋቂ አትሌቶች በውይይቱ ላይ ተሳትፈዋል።