ቀጥታ፡

የአፍሪካ ቢዝነስ ካውንስል የአፍሪካን ነጻ የንግድ ቀጣና ትግበራ በግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳለጥ ይሰራል-ዶክተር አሚናይ አስፎር

አዲስ አበባ(ኢዜአ) የካቲት 17/2015 የአፍሪካ ቢዝነስ ካውንስል የአፍሪካን ነጻ የንግድ ቀጣና ትግበራ በግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳለጥ እንደሚሰራ የተቋሙ ፕሬዝዳንት ዶክተር አሚናይ አስፎር ገለጹ።

ባሳለፍነው ሳምንት 36ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ''የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ትግበራን ማፋጠን'' በሚል መሪ ሃሳብ መካሄዱ ይታወሳል።

በጉባኤው የተሳተፉ የአፍሪካ ቢዝነስ ካውንስል ፕሬዝዳንት ዶክተር አሚናይ አስፎር ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣናው እውን እንዲሆን የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ወሳኝ ነው።

በአህጉሪቷ በግሉ ዘርፍ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ባለሃብቶች ሰፊ ኃብት የሚያንቀሳቅሱ መሆኑን ገልጸው የገበያ ትስስራቸው ግን ከአህጉሪቷ ውጪ ከሌሎች አገራት ጋር መሆኑን ይናገራሉ።

ይህንን አካሄድ በመለወጥ ከአፍሪካ አገራት ጋር ያለውን እርስ በእርስ የንግድ ልውውጥ ለማጠናከር መሥራት እንደሚገባ ጠቁመው በዚህም የግሉ ዘርፍ መሪ ተዋናይ መሆን አለበት ነው ያሉት።

በግሉ ዘርፍ ተሳትፎ የንግድ ቀጣናው እውን ለማድረግ የጥሬ እቃ አቅርቦት፣ ምርትና ምርታማነት ማስፋት፣ ደረጃው የጠበቀ ምርት ማምረትና የኢንዱስትሪ ዘርፉን ማሳደግ እንደሚገባ አስረድተው ለዚህም የአፍሪካ ቢዝነስ ካውንስል ድጋፉ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

በተጨማሪም የነጻ የንግድ ቀጠናው ለማሳለጥ በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።

በአህጉሪቷ ኢትዮጵያን ጨምሮ 17 አገራት የአፍሪካ አንድ ወጥ የአየር ትራንስፖርት /ሳትም/ ገበያን በሙከራ ደረጃ ለመጀመር መስማማታቸው ይታወሳል።

ሥምምነቱ በአገራቱ መካከል የሚደረጉ በረራዎች ያለባቸውን ገደብ የሚያስቀርና ገበያቸውን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ለሌላኛው እንዲከፍቱ የሚያስችል ሲሆን የአፍሪካ ቢዝነስ ካውንስልም በሥሩ ባሉት ሴክተሮች አማካኝነት፣ ለዚሁ ትግበራ እውን መሆን የሚረዱ ተቋማዊ ግንኙነቶችን እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

የአፍሪካ አንድ ወጥ የአየር ትራንስፖርት ትግበራ የሚደነቅ መሆኑን አንስተው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዚህ ረገድ ጉልህ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2018 በሩዋንዳ መዲና ኪጋሊ በተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት አስቸኳይ ስብሰባ ነው ተግባራዊ እንዲሆን ውሳኔ የተላለፈው።


አሁን ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ 46 የሚደርሱት አገራት በሕግ መወሰኛ ምክር ቤቶቻቸው አፅድቀውታል።

የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ታህሳስ 23/2015 ዓ.ም ጀምሮ ይፋዊ ግብይቱን ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም