ቀጥታ፡

ተንቀሳቃሽ የቅርስ አውደ ርዕይ በሐረር ከተማ ተከፈተ

ሐረር(ኢዜአ) የካቲት 17/2015 የሙዚየሞችን እንቅስቃሴ ለማበረታታት ዓላማ ያደረገ ተንቀሳቃሽ የቅርስ አውደ ርዕይ በሐረር ከተማ በሚገኘው የሐረሪ ባህል ቤት ዛሬ ተጀምሯል።

አውደ ርዕዩ በከተማዋ ሲካሄድ ከ2012 ዓ.ም. በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ተገልጿል።

በኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን የብሔራዊ ሙዚየም ዳይሬክተር አቶ ደምረው ዳኜ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በዋናነት ከተጎዱት ተቋማት መካከል ሙዚየሞች ቅድሚያውን እንደሚይዙ ገልጸዋል።

አውደ ርዕዩ በክልሎች እና ሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ የሙዚየሞችን እንቅስቃሴ ለማበረታታት ዓላማ ያደረገ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም ዜጎች አዲስ አበባ ድረስ ሄደው ማየት የማይችሏቸውን ቅርሶች በቀላሉ እንዲመለከቷቸው አማራጭ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

የሐረሪ ክልል ባህል፣ቱሪዝምና ቅርስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተወለዳ አብዶሽ በበኩላቸው "አውደ ርዕዩ በሙዚየም ውስጥ የሚገኙ ቅርሶች በተጠናከረና በተደራጀ መልኩ እንዲቀመጡ እገዛ ያደርጋል" ብለዋል።

"ሐረር ከፍተኛ የሙዚየም ቁጥር ያላት ከተማ ናት" ሲሉ ገልጸዋል።

"ቅርሶቻችን ለሀገራችን ዘላቂ ሰላምና ልማት" በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀው አውደ ርዕይ ዛሬን ጨምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ይቆያል።

አውደ ርዕዩን የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን እና የሐረሪ ክልል ባህል፣ቱሪዝምና ቅርስ ቢሮ በመተባበር አዘጋጅተውታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም