የመከላከያ ሠራዊት አባላትና የመከላከያ ሚኒስቴር ሲቪል ሠራተኞች የኢትዮጵያ ኮሪያ ዘማቾች መታሰቢያ ፓርክን ጎበኙ - ኢዜአ አማርኛ
የመከላከያ ሠራዊት አባላትና የመከላከያ ሚኒስቴር ሲቪል ሠራተኞች የኢትዮጵያ ኮሪያ ዘማቾች መታሰቢያ ፓርክን ጎበኙ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 17/2015 የመከላከያ ሠራዊት አባላትና የመከላከያ ሚኒስቴር ሲቪል ሠራተኞች 127ኛውን የአድዋ ድል በዓል ምክንያት በማድረግ የኢትዮጵያ ኮሪያ ዘማቾች መታሰቢያ ፓርክን ጎበኙ።
ኢትዮጵያ በኮሪያ ጦርነት እንድትሳተፍ በተመድ በቀረበላት ጥያቄ መሠረት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከግንቦት 1950 እስከ ሐምሌ 1953 በተካሄደው ጦርነት ላይ 658 ሠራዊት አሰማርታ በጀግንነት ለዓለም ሰላምና ነፃነት ተዋግታለች።
ወታደሮቹ በ32ኛ ሬጅመንት 7ኛው የአሜሪካ ዲቪዚዮን ሥር ሆነው በሻንያንግኒ አጠገብ በቾኩንሳን ካነግዎን ግዛት ሸለቆዎች በተካሄዱ 253 ጦርነቶች ተሳትፈዋል።
ጦሩ ከኮሪያ ሪፐብሊክ እና ከአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች የክብርና የጀግንነት ሜዳይ ተሸልሟል።
የቃኘው ሻለቃ ጦር እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከመስከረም 16 እስከ 21 ቀን 1951 በሙንዳግ-ኒ ለተደረገው ጦርነት በአሜሪካን ፕሬዚዳንት እንዲሁም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ግንቦት 20/1953 በቾልዎን ሰሜን ምዕራብ ለተደረገው ጦርነት በኮሪያ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ተሸልሟል።
ወደ ኮሪያ የዘመተው የኢትዮጵያ ጦር ከያዘው መሬት አንድ ኢንች እንኳ ያልሰጠና አንድም ወታደር በምርኮ ያልተወሰደበት ጦር ነበር።
ኢትዮጵያውያን የሀገራቸውን ልዩና ከፍተኛ የውጊያ ችሎታ ያሳዩበት ነው የሚለውን ሐሳብ ያረጋገጡበት ነው።
በዚህም "በክብር እንደሰጠናችሁ በክብርና በድል ይዛችሁ ተመለሱ" ተብለው የተሰጣቸውን ኃላፊነት በተግባር ፈፅመዋል።