ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ በኢንደስትሪ ፓርክ አልሚነት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 17/2015 የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ በኢንዱስተሪ ፓርክ አልሚነት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።

ስምምነቱን የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዳንኤል ተሬሳ እና የኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ዋና ስራ አስፈጻሚ ብሩ ወልዴ ፈርመውታል።

በስምምነቱ መሰረት ፕሮጀክቱ በቢሾፍቱ አካባቢ ከ100 ሚልዮን ዶላር በላይ የኢንቨስትመንት ካፒታል እንደሚከናወን ተገልጿል።

የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዳንኤል ተሬሳ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የተለያዩ የፓሊሲ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ በማድረግ ከፍተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት መሳብ መቻሉን ገልጸዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት 2 ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት መሳብ መቻሉን ተናግረዋል።

ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ከፍተኛ ልምድ ያለው መሆኑን ገልጸው የሀገር ውስጥ ምርቶችን በማስተዋወቅ እና የምርት ትስስርን በማጠናከር በኩል ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቱ በስምምነቱ መሰረት በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ አቶ ዳንኤል ተናግረዋል።

የኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ብዙአየሁ ታደለ በበኩላቸው ፓርኩ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ ለ 15 ሺህ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

ፓርኩ በአይነቱ የተለየና በሀገር ውስጥ ባለሀብት የሚለማ መሆኑም የተለየ እንደሚያደርገው ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቱ በ20.6 ሄክታር መሬት ላይ በስራ ላይ ያለና በከተማ መስተዳደሩ በተሰጠው 80 ሄክታር ቦታ ላይ የሚተገበር ፕሮጀክት መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም