የኢትዮጵያና ኡጋንዳ የፓርላማ አባላት በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ በትብብር ስለሚሰሩበት ሁኔታ መከሩ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያና ኡጋንዳ የፓርላማ አባላት በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ በትብብር ስለሚሰሩበት ሁኔታ መከሩ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 17/2015 የኢትዮጵያና ኡጋንዳ የፓርላማ አባላት ሀገራቱ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ በትብብር ስለሚሰሩበት ሁኔታ ምክክር አካሂደዋል።
በኡጋንዳ የፓርላማ አባል አሲመዊ ፍሎሬንስ ሰብሳቢነት የተመራው የኡጋንዳ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሰው ኃብት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጋር በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ በትብብር ስለሚሰሩበት ሁኔታ ተወያይቷል።
የልኡካን ቡድኑ ሰብሳቢ አሲመዊ ፍሎሬንስ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት የሀገሪቱ ፓርላማ አንድ ምክር ቤት ብቻ ያለው ሲሆን የፓርላማ አባላቱም 529 እንደሆኑ አስረድተዋል።
የሀገሪቱ ፓርላማ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን እንደሚያካትት አስገንዝበው በካቢኔ ደረጃ የህገ-መንግስት ጉዳዮች ሚኒስትርም የተቃዋሚ ፓርቲ አባል እንደሆነም ለሰው ኃብት ልማት፣ ስራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ገልፀዋል።
በቀጣይ ከኢትዮጵያ የፓርላማ አባላት ጋር በሳይንስ፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ እንዲሁም ሁለቱን ሕዝቦች ሊያዘምኑ እና ሊያሳድጉ በሚችሉ ጉዳዮች ዙሪያ የተለያዩ ልምዶችን በመለዋወጥ በጋራ መስራት እንደሚገባቸው ነው ያስረዱት።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ኃብት ልማት፣ ስራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል የተከበሩ ሩቂያ አልይ (ዶ/ር) ለልዑካን ቡድኑ አባላት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር አድርገዋል።
የኮሚቴውን ዝርዝር ኃላፊነት እና ተግባር ገለፃ አድርገው፤ የምክር ቤቱን አውቃቀር እና አደረጃጀት አስመልክቶ ከልዑካን ቡድኑ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የኡጋንዳ የፓርላማ የልዑካን ቡድን አባላት የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ሲሆኑ ወደ ኢትዮጵያ ፓርላማ የመጡበት ዋና ዓላማም የኢትዮጵያ ፓርላማ የክትትል እና ቁጥጥር ስራው ምን እንደሚመስል ልምድ ለመቅሰም እንደሆነም ዶክተር ሩቂያ ተናግረዋል።
ዶክተር ሩቂያ አያይዘውም የሁለቱም ሀገራት ምክር ቤቶች ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ጭምር እንደሚያሳትፉ እንዲሁም በሚኒስትር ደረጃ እንደሚሾሙ እና ይህም የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታውን ሂደት እንደሚያሳይ አብራርተዋል።