ቀጥታ፡

ፈረንሳይ ብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን የሚያከናውናቸውን ስራዎች ለመደገፍ ቃል ገባች

አዲስ አበባ(ኢዜአ) የካቲት 17/2015 ፈረንሳይ ብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን ለሚያከናውናቸው ስራዎች ስኬታማነት ድጋፍ እንደምታደርግ ገለጸች።

ብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ሲካሄዱ የቆዩት ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ የመጨረሻ እልባት እንዲያገኙ ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ የተቋቋመ ኮሚሽን ነው።

በተደራጀ ኃይል ውስጥ ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ኃይሎች ትጥቃቸውን ፈተው ወደ ማህበረሰቡ በዘላቂነት እንዲቀላቀሉና ሰላማዊ ኑሮ መምራት እንዲችሉ ለማድረግ፣ በኢትዮጵያ የልማት፣ የሰላም እና የዲሞክራሲ ግንባታ ሂደት እንዲሳተፉ ለማስቻል የተቋቋመ ነው።

የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ እና ከኤምባሲው ወታደራዊ አታሼ ኮሎኔል ጄን ማርክ ጋር ተወያይተዋል።

አምባሳደር ተሾመ ቶጋ የኮሚሽኑ የዝግጅት ምዕራፍ እና ከልማት አጋሮች ጋር በጋራ ስለሚከናወኑ ስትራቴጂያዊ የአጋርነትና ትብብር ስራዎች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን ስራዎች እንዲሳኩ የበኩላቸውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ቃል መግባታቸውን ከሰላም ሚኒስቴር ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም