ቀጥታ፡

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ15ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ሁለተኛ ቀን ውሎ

አዲስ አበባ የካቲት 17/2015(ኢዜአ) ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 15ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

በድሬዳዋ ስታዲየም ከቀኑ 10 ሰአት ሀዲያ ሆሳዕና ከኢትዮጵያ መድን ይጫወታሉ።

ሀዲያ ሆሳዕና በፕሪሚየር ሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው 14 ጨዋታዎች አምስት ጊዜ አሸንፏል። ሶስት ጊዜ ሽንፈት ገጥሞታል። ስድስት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።

በ14ቱ ጨዋታዎች 12 ግቦችን ሲያስቆጥር 8 ጎሎች ተቆጥረውበታል። በአራት የግብ ክፍያ በ21 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል።

ተጋጣሚው ኢትዮጵያ መድን በበኩሉ በዘንድሮው የውድድር ዓመት ጥሩ ግስጋሴ በማድረግ ላይ ይገኛል።

እስከ አሁን በሊጉ ባደረጋቸው 14 ጨዋታዎች ስምንቱን አሸንፏል። ሶስት ጊዜ ተሸንፎ ሶስት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።

ኢትዮጵያ መድን 26 ግቦችን ሲያስቆጥር 21 ግቦች ተቆጥረውበታል። በአምስት የግብ ክፍያ በ27 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በሌላኛው የ15ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ለገጣፎ ለገዳዲ ከመቻል ከምሽቱ 1 ሰአት ላይ ይጫወታሉ።

በፕሪሚየር ሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተሳተፈ የሚገኘው ለገጣፎ ለገዳዲ ጥሩ የውድድር ዓመት እያሳለፈ አይገኝም።

በሊጉ እስከ አሁን ካደረጋቸው 14 ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። 10 ጊዜ ተሸንፏል። ሶስት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።

ብቸኛ የሊግ ድሉን ያስመዘገበው በመጀመሪያ ሳምንት ሐዋሳ ከተማን 2 ለ 1 ባሸነፈበት ጨዋታ ነው።

ለገጣፎ ለገዳዲ በ14 ጨዋታዎች 10 ግቦችን ሲያስቆጥር 34 ግቦችን አስተናግዷል። በ24 የግብ እዳ የመጨረሻውን ደረጃ ይዟል።

ተጋጣሚው መቻል የውድድር ዓመት ጉዞው አመርቂ የሚባል አይደለም።

እስከ አሁን በሊጉ ባደረጋቸው 14 ጨዋታዎች አራት ጊዜ ሲያሸነፍ አምስት ጊዜ ተሸንፏል። አምስት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።

በ14 ጨዋታዎች 15 ግቦችን ሲያስቆጥር 17 ጎሎች ተቆጥረውበት በሁለት የግብ እዳ በ17 ነጥብ 13ኛ ደረጃን ይዟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም