ቤአኤካ ጠቅላላ የንግድ ሥራ እና ሻክማን የተባለ የውጭ ኩባንያ በኢትዮጵያ ከባድ ተሽከርካሪዎችን መገጣጠም ሊጀምሩ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ቤአኤካ ጠቅላላ የንግድ ሥራ እና ሻክማን የተባለ የውጭ ኩባንያ በኢትዮጵያ ከባድ ተሽከርካሪዎችን መገጣጠም ሊጀምሩ ነው
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 16/2015 ቤአኤካ ጠቅላላ ንግድ ሥራ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር እና ሻክማን ከተባለ ዓለም ዓቀፍ የአውቶሞቲቭ አምራች ኩባንያ በኢትዮጵያ ከባድ ማሽነሪዎችና ተሽከርካሪዎችን መገጣጠም ሊጀምሩ ነው።
የሁለቱ ኩባንያዎች በጋራ ስራ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር በአዲስ አበባ ወዳጅነት ፓርክ ተካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የቤአኤካ ጠቅላላ የንግድ ሥራ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሚካኤል ካሣ፤ ከሻክማን ግሩፕ ጋር በመተባበር ማሽነሪዎችና ተሽከርካሪዎችን የመገጣጠም ስራው ይከናወናል ብለዋል።
በሦስት የትግበራ ምዕራፍ የተከፋፈለ የትግበራ ስምምነት መደረጉን አስታውሰው በመጀመሪያ ዙር በዓመት 1 ሺህ 500 ከባድ ተሽከርካሪዎችን በመገጣጠም ለገበያ እናቀርባለን ነው ያሉት።
በሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ በዓመት 3 ሺህ ተሽከርካሪዎችን የመግጠም አቅድ መያዙን ጠቅሰዋል።
ከተሽከርካሪ መገጣጠምና ማምረት በተጨማሪ የዕውቀትና የሙያ ክህሎት ሽግግርና የሰው ኃይል ሥልጠና ይከናወናል ብለዋል።
ከሚገጣጠሙት መካከል ካሶኒ፣ ሎቤድ፣ የፍሳሽ ጭነት ተሽከርካሪ ሃይቤድ ከባድ ተሽከርካሪዎች መሆናቸውን ጠቅሰው ከ45 ቀናት በኋላ ለገበያ ማቅረብ እንጀምራለን ሲሉ ተናግረዋል።
በስነ-ሥርዓቱ ላይ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፣ የሻክማን ግሩፕ የሥራ ኃላፊዎች እና ሌሎችም ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።