ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሲቪል አቬየሽን ባለሥልጣን የግሉ ዘርፍ በአነስተኛ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ዘርፎች እንዲሰማራ ጥሪ አቀረበ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 16/2015፦ የኢትዮጵያ ሲቪል አቬየሽን ባለሥልጣን የግሉ ዘርፍና የክልል መስተዳደሮች በአነስተኛ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ላይ እንዲሰማሩ ጥሪ አቀረበ።

የኢትዮጵያ ሲቪል አቬየሽን ባለሥልጣን የሲቪል አቬየሽን ዘርፍ አሁን ላይ ያለበትን ደረጃ በተመለከተ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል።


መግለጫውን የሰጡት የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግስቴ በኢትዮጵያ የሲቪል አቬየሽኑ ዘርፍ ተደራሽነት ውስንነት ያለበት ነው ብለዋል።


ከዚህ በፊት የአቬየሽኑ ዘርፍ ተግባር በአመዛኙ በፌደራል መንግሥት የሚከናወን መሆኑን አንስተው አሁን ላይ የግሉ ዘርፍ እንዲሳተፍ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።


ለዚህም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሃብቶችና ክልሎች ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው የግሉ ዘርፍና ክልሎች በሲቪል አቬየሽን ኢንዱስትሪው ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።


አሁን ላይ እንደ አገር አራት ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ደረጃ የተሰጣቸውን ጨምሮ ሃያ ሁለት መደበኛ አገልግሎት የሚሰጡ የአየር ማረፊያዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።


በተጨማሪም አነስተኛ የአውሮፕላን ማረፊያዎች ለሜጋ ፕሮጀክቶች፣ ለማዕድን ማውጣት፣ ለግብርና፣ ለመዝናኛና ለሰብዓዊ እርዳታ አገልግሎት የሚውሉ መኖራቸውን ገልጸዋል።


እነዚህ አነስተኛ የአውሮፕላን ማረፊያዎች ከአጠቃላይ የህዝብ ቁጥር አንጻር ሲታይ እጅግ ጥቂት በመሆኑ ተደራሽነት ላይ ውስንነት እንዲኖር ማድረጉን ተናግረዋል።

በመሆኑም መንግሥት የግል ባለ ሀብቱና የክልል መስተዳደሮችን በዘርፉ በማሳተፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ተደራሽነቱን ከፍ ለማድረግ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም