ቀጥታ፡

የኮማንዶ እና አየር ወለድ ጀግኖች ገድልና የጀግንነት ታሪክ ተፅፎ ለትውልድ ሊተላለፍ ይገባል- ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 16/2015 የኮማንዶ እና አየር ወለድ ጀግኖች ገድልና የጀግንነት ታሪክ ተፅፎ ለትውልድ ሊተላለፍ ይገባል ሲሉ የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ፡፡

በሀገራዊ ግዳጅ ላይ ለቆዩ የኮማንዶ እና የአየር ወለድ ዕዝ አባላትና የጦር መኮንኖች በቡልቡላ ወታደራዊ ማሰልጠኛ የጀግና አቀባበል ተደርጎላቸዋል።  

የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ በዚህ ወቅት "ኮማንዶ እና አየር ወለድ ኃይል አካላዊ ብቃቱ፣ ፅናቱ፣ ወታደራዊ ዕውቀቱና ለሀገሩ በቁርጠኝነትና ታማኝነት የታወቀ የውጊያ የማርሽ ቀያሪ፤ መለያውም የጀግኖች ምልክት ነው" ብለዋል።

 ባለቀይ መለዮዎች "የህዝብ ኩራት፣ አለኝታና መከታ የሆኑ ኃይል ናቸው" ያሉት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ፤ ለዚህ ደግሞ በግዳጅ ላይ የነበሩ ገድሎች ምስክር ናቸው ብለዋል።

 ወደፊትም የበለጠ ለማጠናከር በዕዙ ላይ ኢንቨስት እናደርጋለን ነው ያሉት።  የኮማንዶ እና አየር ወለድ ጀግኖች ገድልና ጀግንነት ታሪክ ተፅፎ ለትውልድ መተላለፍ እንዳለበትም ገልፀዋል። 

"ኢትዮጵያ አለቀላት በተባለ ጊዜ ዋጋ ከፍላችሁና ሀገር አፅንታችሁ በመመለሳችሁ ኢትዮጵያ ታመሰግናችኋለች" ብለዋል።  በቀጣይም ኢትዮጵያ ከሚቃጣባት ጥቃት ሁሉ ለማዳን ትግል ለማድረግ ዝግጅትና ብቃት ግንባታ ያስፈልጋል ብለዋል።

 "ኢትዮጵያን መጠበቅ የሚያልቅ ኃላፊነት አይደለም" ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ በመሆኑም በቀጣይ ወታደራዊ ብቃቱን ለማረጋገጥ የሚያገለግሉ ዝግጅቶችና ተግባራትን ማከናወን እንዳለባቸው አሳስበዋል።

 የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ሹማ አብደታ፤ የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ ሀገርን በማዳን ተልዕኮ አኩሪ ድል ተጎናፅፏል ብለዋል። 

የጦር ክፍሉ ከሌሎች ክፍሎች ጋር በመሆን በሁሉም ግንባሮች ግዳጁን በብቃት ፈፅሞ የተመለሰ መሆኑን ገልፀዋል።  

የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ በአነስተኛ የሰው ኃይል ትልልቅ ግዳጆች ወስዶ በአስቸጋሪና ፈታኝ መልክዓ ምድሮች በመሰማራት ታሪክ ሰርቷል ነው ያሉት። 

በቀጣይም አቅሙንና ቴክኒካዊ ብቃቱን እያሳደገ ይቀጥላል ብለዋል።

 የዕዙ አባላት ለሀገር እና ለህዝብ መስዕዋትነት በመክፈል ወርቃማ ታሪክ ሰርተዋል፤ ወደፊትም በኢትዮጵያ ላይ የሚቃጣ ማንኛውንም ጥቃት በመመከት ጠላቷን ልክ ለማስገባት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም