ወጣቱ ትውልድ ጀግኖች አባቶቻችን በአድዋ ጦርነት ወቅት የፈፀሙትን አኩሪ ድል በልማት ሥራዎች ሊደግመው ይገባል-የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር አባላት - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቱ ትውልድ ጀግኖች አባቶቻችን በአድዋ ጦርነት ወቅት የፈፀሙትን አኩሪ ድል በልማት ሥራዎች ሊደግመው ይገባል-የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር አባላት
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 16/2015 ወጣቱ ትውልድ ጀግኖች አባቶቻችን በአድዋ ጦርነት ወቅት የፈፀሙትን አኩሪ ድል በልማት ሥራዎች ላይ ሊደግመው ይገባል ሲሉ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር አባላት ተናገሩ።
ዘንድሮ ለ127ኛ ጊዜ የሚከበረው የአድዋ ድል በዓል “አንድነት፣ ጀግንነትና ጽናት” በሚል መሪ ሃሳብ በድምቀት እንደሚካሔድ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በአድዋ ጦርነት ጀግኖች አርበኞችና የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከተጎናፀፉት ድል ወጣቱ ትውልድ ሊወስድ የሚገባውን ተሞክሮ አስመልክቶ አባት አርበኞችን አነጋግሯል።
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን የአድዋ ጦርነት መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የአገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር ትልቅ ተጋድሎ የፈፀመበት ነው ብለዋል።
ይህ ድል ከኢትዮጵያ አልፎ የመላ አፍሪካውያን ኩራት እንዲሆን ያደረገው ደግሞ አባቶቻችን የአገራቸውን ነፃነትና ክብር ለማስጠበቅ በጽናት በመታገላቸው እንደሆነም ነው የተናገሩት።
በመሆኑም ወጣቱ ትውልድ አባቶቹ የአገር ሉዓላዊነትና ነፃነትን ለማስጠበቅ በነበራቸው ጽኑ አቋም የተቀዳጁትን አኩሪ ድል በአገር ልማትና እድገት ላይ መድገም ይገባዋል ብለዋል።
አርበኛ አስማማው መከተ በበኩላቸው፤ በአድዋ ጦርነት ወቅት ጀግኖች አባቶች አንድነታቸውን በማጠናከር የጠላትን ጦር በመመከት አኩሪ ገድል ፈጽመዋል።
የአሁኑ ትውልድም ከአባቶቹ አኩሪ ገድል ተሞክሮ በመውሰድ በተለይም በልማት ሥራ ላይ በመሰማራት ለራሱ፣ ለቤተሰቡና ለአገሩ ደጀን መሆን አለበት ብለዋል።
አባቶቻችን በአድዋ ጦርነት ሕይወታቸውን ሰውተው ኢትዮጵያን እንዳቆሙ ሁሉ የአሁኑ ትውልድም አገርን የማስቀጠል ኃላፊነት አለበት ያሉት ደግሞ ሃምሳ አለቃ ዲባባ ጫላ ናቸው።
ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአገር አንድነትና በሉዓላዊነት ጉዳይ ላይ በጋራ ሊቆም እንደሚገባ አሳስበው በተለይም ኢትዮጵያና ሕዝቧን በሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ መሰማራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
በ2014ዓ.ም 126ኛው የአድዋ ድል በዓል “አድዋ ለኢትዮጵያውያን ኅብረት ለአፍሪካ የነፃነት ጮራ’’ በሚል መሪ ሃሳብ መከበሩ ይታወሳል።