ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ፓኪስታን 'ካራቺ' የሚያደርገው የቀጥታ በረራ የሁለቱን አገራት የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ያጠናክራል - አምባሳደር ሻዛብ አባስ

አዲስ አበባ (ኢዜአ)የካቲት16/2015 የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ፓኪስታን ካራቺ ከተማ የሚያደርገው የቀጥታ በረራ የሁለቱን አገራት የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚረዳ በኢትዮጵያ የፓኪስታን አምባሳደር ሻዛብ አባስ ተናገሩ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ መጋቢት 17/2015 ዓ.ም ወደ ፓኪስታኗ ከተማ ካራቺ የቀጥታ በረራ እንደሚጀመር ተገልጿል።

በኢትዮጵያ የፓኪስታን አምባሳደር ሻዛብ አባስ፤ ለኢዜአ እንደገለጹት የሚጀመረው በረራ የአገራቱን ወዳጅነት ለማጠናከር ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል።

የሁለቱን አገራት ኢኮኖሚያዊ ትስስር በማሳደግ የአገራቱን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም ነው ያስረዱት።

በየዓመቱ በርካታ ዜጎች ከፓኪስታን ወደ አፍሪካ እንደሚጓዙ ጠቅሰው፤ አየር መንገዱ የሚጀምረው በረራ ጉዟቸውን ይበልጥ እንደሚያሳልጠው ጠቁመዋል።

ያም ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚጀምረው የቀጥታ በረራ አገራቸው ከአፍሪካ ጋር ያላትን ትስስር ለማጠናከር ያስችላል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያና የፓኪስታን የሁለትዮሽ የንግድ ልውውጥ አሁን ላይ 75 ሚሊየን ዶላር እንደሚጠጋ ጠቁመው ይህንንም ለማሳደግ በረራው ትልቅ አቅም ይሆናል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከፓኪስታን የስኳር ምርቶችን፣ ሩዝ፣ እቃ ማያዣ ቦርሳዎች፣ የህክምና ግብዓቶችን ስታስገባ በአንጻሩ እህሎች፣ የሻይ ቅጠል፣ ቅመማ ቅመም፣ ጨርቃ ጨርቆችን ትልካለች።

በረራው ፓኪስታናዊያን ስለኢትዮጵያና አፍሪካ አገራት ያላቸውን ግንዛቤ እንዲያጎለብቱ በማድረግ በንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ ትልቅ እድል እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል የፓኪስታን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ጠቁመዋል።

በቅርቡ የፓኪስታን ባለሃብቶች ልዑክ ቡድን በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለማየት የመስክ ጉብኝት እንደሚያደርጉ አምባሳደሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ145 በላይ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች አሉት።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም