አየር መንገዱ ከአዲስ አበባ-አቢጃን-ኒው ዮርክ የሚያደርገውን የቀጥታ በረራ በድጋሚ ሊጀምር ነው - ኢዜአ አማርኛ
አየር መንገዱ ከአዲስ አበባ-አቢጃን-ኒው ዮርክ የሚያደርገውን የቀጥታ በረራ በድጋሚ ሊጀምር ነው
አዲስ አበባ(ኢዜአ) የካቲት 16/2015 የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ-አቢጃን-ኒው ዮርክ የቀጥታ በረራ ከግንቦት 21 ቀን 2015 ጀምሮ በድጋሚ እንደሚጀምር አስታወቀ።
በረራው እ.አ.አ ከሰኔ 2019 ጀምሮ የነበረ ቢሆንም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት እ.አ.አ መጋቢት 2020 መቋረጡን አመልክቷል።
ወደ ኒው ዮርክ የሚደረገው የቀጥታ በረራ በድጋሚ እ.አ.አ ጥቅምት 2020 በቶጎ ሎሜ በኩል ተጀምሮ እንደነበር ገልጿል።
ግንቦት 21 ቀን 2015 ዓ.ም በሚጀመረው የአዲስ አበባ- አቢጃን-ኒው ዮርክ የቀጥታ በረራ በሳምንት ለአራት ቀናት እንደሚደረግ አየር መንገዱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው “ የድጋሚ በረራው መጀመር አስደሳች ነው፤ ለመንገደኞችም ተጨማሪ አማራጭ የሚሰጥ ነው” ብለዋል።
በረራው በአሜሪካ እና በአፍሪካ መካከል ያለውን የአየር ትራንስፖርት ትስስር ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን አመልክተዋል።
በተያያዘ ዜና አየር መንገዱ ከግንቦት 8 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ወደ አሜሪካዋ አትላንታ ከተማ አዲስ የመንገደኞች በረራ እንደሚጀምር ገልጿል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ130 በላይ ዓለም አቀፍ የመንገደኞች እና የካርጎ መዳረሻዎች እንዳሉት በመግለጫው አመልክቷል።