ቀጥታ፡

ባለፉት ስድስት ወራት 397 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ግንባታ ተከናውኗል--የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 16/2015 ባለፉት ስድስት ወራት 397 ኪሎሜትር የአስፋልት መንገድ ግንባታ መከናወኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ።

አስተዳደሩ ያለፉት ስድስት ወራት የዕቅድ አፈፃፀሙን እና በቀጣይ ስራዎች ላይ ያተኮረ ውይይት አካሂዷል።

ባለፋት ስድስት ወራት ውስጥ የ14 መንገድ ፕሮጀክቶች ግዢ፤ የ19 ግንባታ ቁጥጥር (Consultant) ግዥ ስለመፈጸሙም ተገልጿል።

በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ውስጥ 397 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ግንባታ መከናወኑ ተመላክቷል።

በመደበኛ፣ ወቅታዊ እና ከባድ ጥገና በአጠቃላይ 5ሺህ 123 ኪሎ ሜትር የመንገድ ጥገና ስራ መከናወኑም ተጠቅሷል።

በበጀት አመቱ የመጀመሪያ 6 ወራት ለተከናወኑ የመንገድ ግንባታ እና የጥገና እንዲሁም የግንባታ ቁጥጥር ግዥ ተግባራት 26 ነጥብ 27 ቢሊዮን ብር ወጪ ማድረጉንም አስተዳደሩ ገልጿል።

ባለፉት ስድስት ወራት በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ የፀጥታ ስጋቶች፣ የስራ ተቋራጮች አቅም ማነስ እና የግንባታ ግብዓት እና የውጭ ምንዛሬ እጥረት በግንባታ ፕሮጀክቶች የግንባታ ሂደት ላይ መስተጓጐልን እንደፈጠረበት አስታውቋል።

ከወሰን ማስከበር ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጉዳዮች በርካታ የመንገድ ግንባታዎች እንዲስተጓጎሉ ማድረጉን ከአስተዳደሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

ችግሩን ለመቅረፍ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ቅንጅትና መናበብ እንደሚያስፈልግ አመልክቷል።

የታዩትን ክፍተቶች በመድፈን በቀጣይ ስድስት ወራት በርካታ ስራዎች እንደሚከናወኑ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም