የሕንድ መንግስት የኢትዮጵያ የአካል ድጋፍ አገልግሎትን ለመደገፍ ቃል ገባ - ኢዜአ አማርኛ
የሕንድ መንግስት የኢትዮጵያ የአካል ድጋፍ አገልግሎትን ለመደገፍ ቃል ገባ
አዲስ አበባ(ኢዜአ) የካቲት 16/2015 የሕንድ መንግስት በጤና ሚኒስቴር ስር ለሚገኘው የኢትዮጵያ የአካል ድጋፍ አገልግሎት ለሚያከናውናቸው ስራዎች ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ።
አገልግሎቱ የሰው ሰራሽ አካልና ድጋፍ በመስራት የሚታወቅ ነው።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰና በኢትዮጵያ የሕንድ አምባሳደር ሽሪ ሮበርት ሼትኪንቶንግ የኢትዮጵያን የአካል ድጋፍ አገልግሎት የስራ እንቅስቃሴን ጎብኝተዋል።
የአገልግሎቱ አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴ፣በሰዉ ሰራሽ እና አጋዥ ቴክኖሎጂ እየተመረቱ ካሉት የአካል ድጋፍ የ’ላሚኔሽን’(ማተም) ቴክኖሎጂ እና የጫማ ስራዎች ተመልክተዋል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አገልግሎቱ አዲስ ተቋም ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በአቅርቦት እና በሌሎች ጉዳዮች ዙርያ ተቋሙ ያለበትን ችግር ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን በማንሳት።
ዶክተር ሊያ በኢትዮጵያ የሕንድ አምባሳደር ከአሁን ቀደም ለነበራቸው አጋርነት እና ልዩ ድጋፍ አድናቆታቸውን ገልጸው ተቋሙን በመጎብኘት ተቋሙን በተለያየ መልኩ ለመደገፍ ላሳዩት ቁርጠኝነትም አመስግነዋል።
በሕንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሽሪ ሮበርት ሼትኪንቶንግ በበኩላቸው ተቋሙን በመጎብኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው ያለበትን ችግር ለመቅረፍ በስልጠና፣ በልምድ ልውውጥ፣ በሙያዊ ድጋፍ እና በግብአት እንደሚደግፉ ቃል ገብተዋል።
የኢትዮጵያ የአካል ድጋፍ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ታሪኩ ታደሰ በበኩላቸው ተቋሙ ራሱን በማዘመን በአገር አቀፍ ደረጃ ተደራሽ ለመሆን እየሰራ ነው ብለዋል።
የተለያዩ አካላት ለተቋሙ እያደረጉ ላሉት ድጋፍ ምስጋና ማቅረባቸውን ከጤና ሚኒስቴር የማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።