ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሚቲዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት በጅግጅጋ ከተማ በ30 ሚሊዮን ብር የሚቲዮሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል ሊያስገነባ ነው

ጅግጅጋ (ኢዜአ) የካቲት 16/2015 የኢትዮጵያ ሚቲዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት በጅግጅጋ ከተማ በ30 ሚሊዮን ብር የሚቲዮሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል ሊያስገነባ ነው።

ኢንስቲትዩቱ በደቡብና ደቡብ ምስራቅ የሀገራችን ክፍሎች የነበረው የበጋ የዝናብ ሁኔታ ግምገማና በበልግ የሚጠበቀውን የአየር ሁኔታ ትንበያ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በጅግጅጋ ከተማ አካሂዷል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ እና የኢትዮጽያ የሚቲዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ ኢንስቲትዩቱ ለሚገነባው ማዕከል የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል። 

ማዕከሉ በ250 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚያርፍ ባለሁለት ወለል ህንፃ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። 

የማዕከሉ ግንባታ ከአንድ ዓመት በኋላ ሲጠናቀቅ የሶማሌ እና የሀረሪ ክልሎች፣ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርና የኦሮሚያ ምስራቅና ምዕራብ ሀረርጌ ዞኖችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል። 

ኢንስቲትዩቱ ለእነዚህ አካባቢዎች የሚሰጠውን የሚቲዮሮሎጂ አገልግሎት ለማሻሻልና ወቅቱ የሚጠይቀውን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለማሟላት ታስቦ የሚገነባ ማዕከል መሆኑን ተጠቅሷል። 

በመድረኩ የበጋ ወቅት ግምገማና በሀገር አቀፍ ደረጃና በምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች በበልግ ወቅት በሚኖረው የአየር ሁኔታ ትንበያ ላይ ያተኮሩ የመወያያ ጽሁፎች ቀርበዋል።  

በደቡብ ምስራቅ ዋናኛ የዝናብ ወቅት የሆነው የበልግ ዝናብ መደበኛና ከመደበኛ በታች እንደሚሆን ይጠበቃል ሲሉ የኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ገልጸዋል።  

ዝናቡ ከመደበኛ ወቅቱ ዘግይቶ የሚጀመር እና 35 በመቶ መደበኛ እንደሚሆን የሚቲዮሮሎጂ ትንባያ መረጃ እንደሚያሳይም አመልክተዋል።  

በእነዚህ አካባቢዎች ዋና የዝናብ ወቅታቸው የሆነው የበልግ ዝናብ ዘግይቶ የሚጀምር ብቻ ሳይሆን ከመደበኛ በታች የመሆን እድሎ 50 በመቶ እንደሚሆን ጠቅሰዋል። 

ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም ዝናቡ ወቅቱን ጠብቆ ባለመዝነቡ በአካባቢዎቹ ለሚኖሩ አርብቶ አደሮች የሰውና የእንስሳት የመጠጥ ውሃና የግጦሽ ሳር እጥረት ሊያጋጥም እንደሚችልም ጠቁመዋል።  

በመሆኑም የአካባቢዎቹ ማህበረሰብ ለችግር እንዳይጋለጥ ከወዲሁ የውሃ አቅርቦትን በማሻሻልና የእንስሳት መኖ ክምችት በማዘጋጀት ሁሉም አካላት ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉም አሳስበዋል።  

ኢንስቲትዩቱ በተለያዩ ወቅቶች የሚጠበቀውን የአየር ሁኔታና ፀባይ አሉታዊና አዎንታዊ ሁኔታዎችን አስመልክቶ ቅድመ ማስጠንቀቂያና ምክረ-ሀሳብ ለሚመለከታቸው አካላት እያቀረበ ነው ብለዋል።  

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ በየወቅቱ የሚያቀርበውን የአየር ትንባያ መረጃዎች በመጠቀም የቅድመ መከላከልና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ከክልሎች ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

የዓለም አቀፍ የአየር ሁኔታ መለዋወጥን ተከትሎ የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ አካባቢዎች እያጋጠመ ባለው የዝናብ ስርጭት መቆራረጥ ሳቢያ የውሃ እጥረት እንደሚያጋጥም ጠቅሰዋል። 

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሊያጋጥም የሚችለውን ችግር አስቀድሞ ለመከላከል ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በተፋሰስ ልማት ስራዎች ላይ በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።  

በምክክር መድረኩ ላይ ከሶማሌና ከሀረሪ ክልሎች፣ ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርና ከኦሮሚያ ምስራቅ ሀረርጌ ዞን የተውጣጡ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም