ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአንደኛ ዙር የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ መካሄድ ይጀምራሉ - ኢዜአ አማርኛ
ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአንደኛ ዙር የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ መካሄድ ይጀምራሉ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 16/2015 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ15ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ዛሬ በሚካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች ይጀመራል።
በድሬዳዋ ስታዲየም አርባ ምንጭ ከተማ ከሐዋሳ ከተማ ከቀኑ 10 ሰአት ይጫወታሉ።
አርባ ምንጭ ከተማ እስካሁን ባደረጋቸው 14 ጨዋታዎች 16 ነጥብ በመሰብሰብ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ተጋጣሚው ሐዋሳ ከተማ ደግሞ በ14 ጨዋታዎች 20 ነጥብ ይዞ 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
በሌላኛው ጨዋታ አዳማ ከተማ ከወልቂጤ ከተማ ከምሽቱ 1 ሰአት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
አዳማ ከተማ እስካሁን ባደረጋቸው 14 ጨዋታዎች 15 ነጥብ ብቻ በማግኘት 14ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
በአንጻሩ ተጋጣሚው ወልቂጤ ከተማ በተመሳሳይ 14 ጨዋታዎችን አድርጎ በ20 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል።
ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አንደኛ ዙር ወድድር የካቲት 19 ቀን 2015 ዓ.ም ይጠናቀቃል።
የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ29 ነጥብ ይመራል።
ኢትዮጵያ መድን በ27 እንዲሁም ባህር ዳር ከተማ በ26 ነጥብ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃን ይዘው ይከተላሉ።
አዳማ ከተማ፣ ኢትዮ ኤሌትሪክ እና ለገጣፎ ለገዳዲ ከ14ኛ እስከ 16ኛ ደረጃን በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።
የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ቶጎዋዊ የቅዱስ ጊዮርጊስ አጥቂ ኢስማኤል ኦሮ-አጎሮ በ14 ግቦች ይመራል።
የወልቂጤ ከተማው አምበል ጌታነህ ከበደ በ10 ግቦች ይከተላል።
ፍቃዱ ዓለሙ ከፋሲል ከነማ፣ ይገዙ ቦጋለ ከሲዳማ ቡና፣ ሐቢብ ከማል ከኢትዮጵያ መድን እና ቢኒያም ጌታቸው ከድሬዳዋ ከተማ በተመሳሳይ ሰባት ግቦችን አስቆጥረዋል።