ቀጥታ፡

የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የታዳጊዎች የአትሌቲክስ ፕሮጀክቶች ሻምፒዮና በድሬዳዋ ከተማ ተጀመረ

ድሬዳዋ (ኢዜአ) የካቲት 15/2015 የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የታዳጊዎች የአትሌቲክስ ፕሮጀክቶች ሻምፒዮና ውድድር ዛሬ በድሬዳዋ ስታዲየም ተጀምሯል።

በሻምፒዮናው ድሬዳዋ እና አዲስ አበባን ጨምሮ ዘጠኝ ክልሎች እንዲሁም በፕሮጀክቶች የታቀፉ እና ዕድሜያቸው 18 እና 16 ዓመት የሆናቸው 400 ተተኪ አትሌቶች ተሳታፊ መሆናቸው ተገልጿል።

የውድድሩ አስተባባሪ አቶ አሸብር ደምሴ አገር አቀፍ ውድድሩ ቀደም ሲል ዕድሜያቸው 20 ዓመት ከሆኑ የፕሮጀክቶች ሰልጣኞች ሻምፒዮና ጋር በጋራ ሲካሄድ አንደነበር ለኢዜአ ገልጸዋል።

"ይህንን በማረም ዕድሜያቸው 18 እና በታች እንዲሁም 16 እና በታች የሆኑትን ለብቻ ለይቶ ውድድሩ እንዲካሄድ ተደርጓል" ብለዋል።

ሻምፒዮናው አገር አቀፍ ተተኪ አትሌቶችን በማፍራት አገራችን በዘርፉ ያላትን ከፍታ ለማስቀጠል ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

እንደ አቶ አሸብር ገለጻ፤ ለአምስት ተከታታይ ቀናት በሚካሄደው ውድድር የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ አትሌቶች ተመልምለው በመጋቢት ወር 2015 ዓ.ም ታንዛኒያ በሚካሄደው የአፍሪካ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያን ወክለው ይሳተፋሉ።

የድሬዳዋ አስተዳደር የወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ፊራኦል ቡልቻ በበኩላቸው ውድድሩ በፕሮጀክት የታቀፉ ታዳጊ ወጣቶች ያሉበትን ደረጃ በመመልከት በቀጣይ የተሻለ ስራ ለማከናወን ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ለውድድሩ ስኬታማነት አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

በመጀመሪያው የኢትዮጵያ የታዳጊዎች የአትሌቲክስ ፕሮጀክቶች ሻምፒዮና የዛሬ ውሎ የሩጫ፣ የዝላይ፣ የጦር፣ የአሎሎ፣ የዲስከስ እና የሌሎች ዘርፎች የማጣሪያ ውድድሮች ተካሄዷል።

ሻምፒዮናው እስከ የካቲት 19 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም